
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
መምሪያው በ2017 የትምህርት ዘመን በክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች ነው ዕውቅና የሰጠው፡፡
የመምሪያው ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በሚሠራበት የትምህርት ተቋም ያልተዘራ እንደማይታጨድ በማመን ተማሪዎቹን ለማብቃት ጥረት ሲደረግ ነበር ብለዋል፡፡
ተሞክሮዎችን በማስፋት ከክፍል መማር ማስተማር ባሻገር ተማሪዎች በማጠናከሪያ ትምህርት ጭምር ሲታገዙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ከ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናውን የወሰዱ 2ሺህ 100 ተማሪዎች፣ ከ8ኛ ክፍል 1ሺ 800 በላይ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 1ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች ውስጥ 23 ነጥብ 5 በመቶ የሚኾኑት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡
ለዚህ ውጤት መመዝገብ ከተማሪዎቹ ጥረት ባሻገር አጠቃላይ የትምህርት መሪዎች፣ መምህራን እና ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በኀይሉ ገብረ ሕይወት ትምህርት ከችግሮች መውጫ መንገድ መኾኑን መገንዘብ አስፈላጊ እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት እና ደረጃ በማሻሻል፣ ግብዓቶችን በማሟላት እና ጥራቱ እንዲጠበቅ በማስቻል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የቀጣይ ትኩረት መኾን አለበት ብለዋል፡፡
በቅንጅት በተሠሩ ሥራዎች በባለፈው የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አንስተው በቀጣይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እንደ ኃይሌ ማናስ እና ኃይለማሪያም ማሞ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለመፍጠር ተሞክሮዎችን ማስፋት ላይ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶችም በቀጣይ ከነበሩበት ችግር እንዲወጡ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና እና ማበረታቻ ሽልማት በሰጠበት መድረክ በባለፈው የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ታድመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
