44 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ለማልማት ማቀዱን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

3
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ የበጋ መስኖ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 44 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል ብለዋል። በመስኖ ከሚለማው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ 1 ነጥብ 67 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል።
ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ለአርሶ አደሮች 180 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 7 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር የተዘጋጀ ሲኾን የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችም ለአርሶ አደሮች መሠራጨታቸውን ተናግረዋል።
ውኃ አጠር አካባቢዎችን በተገቢው መንገድ ለማልማት በ12 ወረዳዎች ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጠብታ መስኖ ይለማል ነው ያሉት።
በዞኑ ከዚህ በላይ ማሳ ማልማት የሚችል የውኃ እና የመሬት ሃብት እንዳለ የተናገሩት አቶ ታደሰ ይህንን ለማልማት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ከመስኖ ሥራው ጎን ለጎን የሚተገበረው ሌላው ሥራ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባር ነው ብለዋል ኀላፊው። በዚህ ዘርፍ 36 ሺህ ሄክታር በአዲስ እና በነባር የሚሠራ ይኾናል ብለዋል። ለዚህም ከ400 ሺህ በላይ የሰው ኃይል ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወሰኔ አንበርብር የመስኖ ሥራን ለማሳደግ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ መሥራት አስፈላጊ በመኾኑ ተግባሩ የማይነጣጠል ነው ብለዋል። በወረዳው ከ1 ሺህ 400 በላይ ሄክታር ማሳም በመስኖ እንደሚለማ ተናግረዋል።
የሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ ግበርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጥላሁን እንዳለማሁ ወረዳው ለስንዴ ምርት ምቹ በመኾኑ በመስኖ ከ1 ሺህ 200 ሄክታር ማሳ በላይ የሚለማ ሲኾን 850 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ የሚለማ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ300 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለው አጓት ውኃ የመስኖ ፕሮጀክት
Next articleዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሠራ ነው።