
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአጓት ውኃ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በደቡብ ጎንደር ዞን በስማዳ ወረዳ ይገኛል። ፕሮጄክቱ በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ገብቷል። የአካባቢው አርሶ አደሮች ይህን ፕሮጀክት ተጠቅመው መስኖ ማልማት ጀምረዋል።
ወጣት ማንደፍሮ ጌትነት የአጓት ውኃ መስኖ ግድብ ተጠቃሚ ነው፡፡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ሥራ ከጀመረበት በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾናቸውን ነግሮናል፡፡
በዓመት ሦስት ጊዜ እያመረቱ መኾኑንም ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጾልናል። በተለይ ስንዴ፣ ሽንኩርት እና ሌሎች አትክልቶችን በማምረት ተጠቃሚ ኾነናል፤ ወጣቶች መሬት ተከራይተው በማልማት የተሻለ ገቢ እያገኘን ነው ብሏል፡፡
ከቤተሰቦቻቸው ጋር የነበሩ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው መሬት በመከራየት እስከ 400 ሺህ ብር ድረስ ከሽንኩርት ብቻ ማግኘት ችለዋል ነው ያለው፡፡ ግድቡ ወደ ሥራ በመግባቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ደስተኛ መኾኑን እና ከሌላ ቦታ መጥተው የሚያለሙ እንዳሉም ገልጿል፡፡
የግድቡ ካናል አለመራዘም እና ግድቡ በደለል የመሞላት ስጋት እንዳለበትም ተናግሯል።
ሌላው ተጠቃሚ አርሶ አደር ሀብታሙ አየነው የመስኖ ግድቡን በመጠቀም በመስኖ እርሻ ሥራ ላይ መሠማራታቸውን ነግረውናል። በዓመት ሦስት ጊዜ ከመደበኛው የሰብል ልማት በተጨማሪ አትክልት በሰፊው በማምረት ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ ግብዓት እጥረት እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ ዘንድሮ ግን የመስኖ ልማቱን ታሳቢ ያደረገ የማዳበሪያ አቅርቦት መግባቱን ገልጸውልናል። በመስኖ ባመረቱት ምርት የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውን እና ሕይዎታቸው እየተለወጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
የስማዳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በለጠ ጠቅል የአጓት ውኃ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በ2009 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል። ፕሮጀክቱ በ3 ዓመታት እንዲጠናቀቅ የታሰበ ቢኾንም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዘግይቶ ነበር ነው ያሉት። በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ 200 ሄክታር መሬት በማልማት 400 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታስቦ መሠራቱን ኀላፊው አንስተዋል። አሁን ላይ 155 ሄክታር መሬት እየለማ ነው። 323 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል። የሚለማው መሬት ስፋት እንደሚጨምርም ገልጸዋል።
በመስኖ ግድቡ አርሶ አደሮች በዓመት ሦስት ጊዜ የመስኖ ሰብሎችን እና አትክልቶችን ማምረት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ድንች የመሳሰሉ በገበያ ላይ ተፈላጊ የኾኑ እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ያመርታሉ ነው ያሉት። በግለሰብ ደረጃ ከሽንኩርት ብቻ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳገኙ እና አርሶ አደሮቹ የተሻለ ተጠቃሚ እንደኾኑም ነው የተናገሩት።
የመስኖ ግድቡ የአርሶ አደሮቹን የሥራ ባሕልም የቀየረ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት እንደታየው ምርቱም የተሻለ ጥራት ያለው እንደኾነ ነው የገለጹት። የገበያ ችግር እንዳላጋጠማቸውም ገልጸዋል።
የመስኖ ልማት በግብርና ሥራው ለበርካታ ወጣቶች በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል እንደፈጠረም ተናግረዋል። ይህም በአካባቢው ያለውን የሥራ አጥ ችግር ለመቀነስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
መስኖው ላይ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች ባለሙያ ተመድቦ በቅርብ ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ያጋጠመውን የግብዓት ችግር በዚህ ዓመት እንዳይከሰት የመስኖ ልማቱን ታሳቢ ያደረገ በቂ አቅርቦት አለ ነው ያሉት።
በመስኖ ግድቡ ወደ ማሳው የሚወስደው ካናል እና የውኃ በር በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል። ካናሉ ባለመራዘሙ ተጨማሪ መሬት ማልማት የሚችለው አቅሙ ዝቅ ብሏል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ በደለል ሳይሞላ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ግድቡን የገነባው የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት መሐንዲስ ቢተው መርሻየ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ርክክብ በ2017 ዓ.ም ተደርጓል ይላሉ። የመጨረሻውን ርክክብ በቅርቡ ለማድረግ የቀሩ ሥራዎችን የማጠናቀቅ ተግባር ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ከአርሶ አደሮች የተነሳውን የውኃ ካናል አለመራዘም ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ በተሰጠው የሥራ ዝርዝር ተሠርቷል።
አሁን ላይ ምንም አይነት የደለል ስጋት እንደማይፈጥርም ገልጸዋል።
የውኃ መውጫ በሮችን ዲዛይኑ ላይ ያለው 50 ቢኾንም ማሻሻያ ተደርጎ እና ተጨምሮ 64 በሮች መሠራታቸውን እና በቂ መኾኑን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ ዘርፍ የግንባታ ክትትል ዳይሬክተር ጌትነት አያሌው የአጓት ውኃ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ እና ብዙ ተጨማሪ ወጭ ወስዶ መጠናቀቁን ገልጸዋል። አሁን ላይ ሥራ ጀምሮ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።
የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ የመጨረሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ነው የገለጹት። ለግድቡ ግንባታ ከ198 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበታል ነው ያሉት።
የካናል ይራዘምልን እና የውኃ መውጫ በሮች በቂ አለመኾንን በተመለከተ የመስኖ ግድቡ ዲዛይን ሲደረግ የውኃው መጠን እና የሚለማውን መሬት ታሳቢ በማድረግ መሠራቱን እና ተቋራጩ በውሉ መሠረት ሥራውን ማጠናቀቁን ነው የተናገሩት።
አሁን የቀረበው ጥያቄ ከታቀደው ውጭ ተጨማሪ መሬት እንዲሸፍን ነው፤ ይህ ደግሞ ካናሉ ቢራዘም እንኳን ውኃው በቂ ስለማይኾን ወደ ግጭት ይወስዳል ነው ያሉት።
የውኃው ካናል መጨረሻ ላይ ወደ ጎርጅ ባለመግባቱ በክረምት ቦዩን ተከትሎ የሚመጣ ጎርፍ በማሳ ላይ ይተኛል ብለዋል። የሚተኛውን ውኃ ለማስቀረት ያለው ሥራ ተቋራጩን አይመለከትም ያሉት ዳይሬክተሩ ጥያቄው ዘግይቶ የመጣ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህን ችግር ለመፍታት ወረዳው በራሱ አርሶ አደሮችን በማሥተባበር በባሕላዊ መንገድ ሊያሠራው ይችላል ነው ያሉት።
የውኃ መውጫ በሮችን አካባቢውን መሠረት ያደረገ ጥናት ተደርጎ በደረጃው መሠረት ነው የተሠራው፤ እሱም በቂ ነው ብለዋል።
ግድቡ እስከ 20 ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ የተገነባ እና የሚጠቅመው ማኅበረሰቡን በመኾኑ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ መሥራት እና ወረዳው በባለቤትነት ይዞ መከታተል አለበት ነው ያሉት። ግድቡ ከመስኖ በተጨማሪ ዓሣ ሃብት ለማልማት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
