
ጎንደር: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል።
በበጋ መስኖ ልማት የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሤ ማለደ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ19 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዷል ብለዋል።
ከ19 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ማሳ መለየቱን የገለጹት ኀላፊው እስካሁንም ከ1 ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።
በዞኑ በመስኖ ልማት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲኾን ከዚህም ከ795 ሺህ 400 በላይ ኩንታል የሚኾነው ምርት ከበጋ መስኖ ስንዴ ለማግኘት ታቅዷል።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ 160 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውንም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።
ለበጋ መስኖ ከ4 ሺህ 500 በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱም ተገልጿል። በቀጣይም 50 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየተጓጓዘ መኾኑም ኀላፊው አስረድተዋል።
ምርጥ ዘር በበቂ ኹኔታ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂ የማላመድ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት ደግሞ የወገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻሌ አዛኔ ናቸው።
በወረዳው በበጋ መስኖ ከ358 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዷል ብለዋል። ከዚህም ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል። ለአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደኾነም ተነስቷል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ሲዘሩ ያገኘናቸው አርሶ አደር አስማው መኮንን እና አርሶ አደር አምባቸው ጸጋየ በልማት ሥራው ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ተናግረዋል።
ለበጋ መስኖ ስንዴ በጋራ እያረሱ መኾኑን የነገሩን አርሶ አደሮቹ ባለፈው ዓመት ከ4 ሄክታር መሬት ከ32 ኩንታል በላይ ስንዴ ማግኝታቸውን አስታውሰዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በንቅናቄ ለመዝራት እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ :- አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
