የምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን ለመመለስ እየሠራ ነው።

6

ፍኖተ ሰላም: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ የአብሥራ ሞላ እና ገዳሙ ጌትነት በፍኖተ ሰላም ቁጥር አንድ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።

ተማሪዎቹ ለመጭው ፈተና ከወዲሁ ራሳቸውን እያዘጋጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። መምህራንም ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት እየሰጡ ናቸው ብለዋል።

የፍኖተ ሰላም ቁጥር አንድ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ተመስገን መኮንን 1 ሺህ 843 ተማሪዎችን በመመዝገብ የመማር ማስተማር ሥራው እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። በተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች በትርፍ ጊዜ ተማሪዎችን ለፈተና የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሌሎች አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተማሪ ዳዊት አስተራይ እና ተማሪ መስከረም ፀጋ ደግሞ የዳሞት ቁጥር ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ከወዲሁ የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ ጊዜያቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አልመው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አንለይ የኔዓለም በትምህርት ዘመኑ ከተማ አሥተዳደሩ 22 ሺህ 20 ተማሪዎችን በመመዝገብ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የመማር ማስተማር ሂደቱን በወቅቱ በማስጀመር ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን በምዕራብ ጎጃም ዞን 426 ሺህ 29 ተማሪዎች መማር ቢኖርባቸውም እስካሁን 89 ሺህ 738 ተማሪዎች ብቻ እየተማሩ መኾናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የስጋት ደሴ ተናግረዋል።

በቀጣይ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል። በዞኑ ካሉ 600 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 498 ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር አለመጀመራቸውን የገለጹት መምሪያ ኀላፊው 161 ትምህርት ቤቶች በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎችን ከመመዝገብ በተጨማሪ ኅብረተሰቡን፣ አጋር እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ መኾኑ ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሥርዓተ ምግብ ሞዴል የኾኑ መንደሮች ተመረቁ።
Next articleየማዕከላዊ ጎንደር ዞን ‎በበጋ መስኖ ልማት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየሠራ ነው።