በሥርዓተ ምግብ ሞዴል የኾኑ መንደሮች ተመረቁ።

5

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ በሥርዓተ ምግብ ሞዴል የኾኑ መንደሮች ተመርቀዋል።

በወረዳው የጎልባ ቀበሌ አርሶ አደሮች የተሻሻለ አመራረት ዘዴ በመጠቀም የተመጣጠነ ምግብ ለቤተሰባቸው መመገብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ሃብቱ እያላቸው ልጆቻቸውን በተገቢው ሁኔታ መመገብ ባለመቻላቸው በተመጣጠነ ምግብ እጦት በድለዋቸው መቆየታቸውን አብራርተዋል።

የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ደረሰ ደመመ የግብርናው ዘርፍ በቁጭት የሚመራ ዘርፍ እንደኾነም አብራርተዋል።

በአርሶ አደሩ ቀየ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እያለ እስካሁን የምግብ ዋስትናውን ባለማረጋገጡ ሥራዎችን በቁጭት ለመሥራት መነሳት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሞዴል የሥርዓተ ምግብ መንደሮቹ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት፣ ታዳሽ ኀይል መጠቀም እና የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት አጠቃቀም እንደሚተገበርባቸውም ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና ምምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ አርሶ አደሮች ሃብቱ በእጃቸው እያለ በአመለካከት ችግር ብቻ ሕጻናት ለመቀንጨር ሲዳረጉ ቆይተዋል ነው ያሉት።

የአንጎለላና ጠራ ወረዳ በምግብ ዋስትና የታቀፈ ቢኾንም አሁን ባለው ጥረት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የሥርዓተ ምግብ ትግበራን በማረጋገጥ ሞዴል መንደር በመፍጠር አርዓያ መኾን ችሏል ብለዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አብርሃም ሙጬ የመቀንጨር ምጣኔው በሀገር ዕድገት እና በማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍተኛ በመኾኑ እንቅልፍ የሚያስተኛ አይደለም ብለዋል።

በአንድ ሀገር የመቀንጨር ምጣኔ 20 በመቶ ከደረሰ በአሳሳቢነት ደረጃ ይፈረጃልም ነው ያሉት።

የጎልባ ቀበሌ ነዋሪዎች ግን የተሰጡትን ትምህርት እና ምክር ወደ ተግባር በመቀየር ሥርዓተ ምግብን በአግባቡ መተግበራቸው ለሌሎችም ትምህርት እንደሚኾን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ለዓለም ለይኩን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና መስጠት ጀመረ።
Next articleየምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን ለመመለስ እየሠራ ነው።