
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥንታዊ ሥልጣኔዋ ከውኃ ጋር የተቆራኘው ኢትዮጵያ የጂኦ ፖለቲካ ቅኝቷ ውኃን መሠረት ያደረገ እንደነበር ይነገራል፡፡ ወደ ውኃ ስትቀርብ ገናና፤ ከውኃ ስትርቅም ኮስማና እንደነበረች ደግማ ደጋግማ ታይታለች፡፡ ይህንን ጠንቅቀው የተረዱት ስትራቴጂክ ተቀናቃኞቿም ኢትዮጵያን ከውኃ ለመነጠል እና ለማራቅ ያልሞከሩት ጦርነት፤ ያላወሳሰቡት ክፋት አልነበራቸውም፡፡
ኢትዮጵያ ለባሕር በር እንግዳ ሀገር አይደለችም፡፡ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የባሕር ላይ ንግድ ውድድሯ ከሮማ እና ግሪክ ኢምፓዮሮች ጋር እንደነበር ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር እና የንግድ መርከቦችን በቀይ ባሕር ላይ አሰማርታ ትጠቀም ነበር፡፡ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊትም በቀይ ባሕር ላይ ጠንካራ የተባለ የባሕር ኀይል ነበራት፡፡ ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የውኃ በር የነበራት ሀገር ፍፁም ዝግ ከተደረገች ከሩብ ምዕተ ዓመት ገፋ ያለ እድሜን ብቻ አስቆጥራለች፡፡
ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትርቅ የተደረገችበት መንገድ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና መልክዓ ምድራዊ አመክንዮ የለውም የሚሉ ተማጋቾች በየጊዜው ቢነሱም ከግለሰባዊ ፍላጎት ትንሽም ቢኾን ፈቀቅ ያላለው የሀገሪቷ የፖለቲካ ባሕል ለጥያቄው ምላሽ “ጆሮ ዳባ ልበስ” የሚሉት ዓይነት ነበር፡፡ በከፍተኛ ሀገራዊ ወጪ የገነባችው ባሕር ኀይል ህልም እስኪመስል ድረስ እንዳልነበር ኾነ፡፡ ከ26 በላይ መርከቦቿ በባዕዳን ሀገር በጥገኝነት ዓመታትን እንዲቆሙ ሲገደዱ ከ17 ሺህ በላይ የባሕር ኀይል ሠራዊቷ እንደ ተራ ነገር ተበተነ ተባለ፡፡ የታሪካዊ መርከቦቿ እጣ ፋንታ በቁርጥራጭ ብረት ተመዝኖ መሸጥ ሲኾን ይህንን መመልከት ለበርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘመን የማይሽረው የእግር እሳት ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ያገባናል ብለው የሞገቱት ግን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ መጻዒውን የሀገሪቷን እጣ ፋንታ ጠንቅቀው የተረዱ የውጭ ዜጎችም ጭምር እንደነበሩ ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ትርፍ እና ኪሳራው ምን እንደኾነ በውል ባልታወቀ መልኩ በወቅቱ ሀገሪቷን የሚመሩ የፖለቲካ ሰዎች “አሰብ በአፍንጫችን ይውጣ” አሉ፡፡ “ግመል ያጠጡበት” ከሚለው ያልተገራ ትርክት ጀምሮ ነገርየው ተራ ብሽሽቅ እስኪመስል ድረስ ወርዶ የባሕር በር ጉዳይን የሚያነሱ ልሂቃን የፖለቲካ ታርጋ ይለጠፍባቸው ጀመር፡፡
በፖለቲካው ሰዎች ዘንድ ፊት የተነሳው የሀገሪቷ የባሕር በር ጥያቄ ሥር ሰድዶ በትውልዱ ዘንድ ቀይ ባሕር እና አሰብ ዳግም ላይነሱ የተረሱ መሰሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ባለቤቶች “መኾን አለብን” ማለቱ ቀርቶ “ነበርን” እንዳይሉም በተጠና መልኩ ገለል ተደረጉ፡፡ ግን ጉዳዩ ፈጽሞ የሚከስም እንዳልነበር በትንቢት መልክ ቀደም ብሎ በጀግኖቿ ተነግሮ ነበር፡፡ የባሕር በር ጉዳይ ዘመን እንደወሰደው ሁሉ ዘመን እንደሚያነሳው በአንዳንድ ፖለቲካዊ ውይይቶች በተለይም በምርጫ ወቅት ዘመቻዎች ማድመጥም የተለመደ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የኢትዮጵያውያንን የባሕር በር ጥያቄ አይቀሬ መኾኑን ቀደም ብለው ከሚያውቁት እና ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ነበሩ፡፡
“ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ቁመታቸው ረዘም ያለ፣ ቀጭን፣ ዐይኖቻቸው ትላልቅ፣ መልካቸው ጠይም፣ ዕድሜያቸው ከ45 የማይበልጥ እና ስፖርተኛ ናቸው፡፡ የ6ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኾነው በ1981 ዓ.ም ወደ ምፅዋ ከመምጣታቸው በፊት የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት በአስመራ የዋልያ ስፖርት ክለብ አዛዥ ነበሩ፡፡ ይህ ሐተታ ሻዕቢያ ከሞታቸውም በኋላ አጥብቆ ለፈለጋቸው ጀግና የጦር መሪ ከቅርብ ረዳቶቻቸው መካከል በአንዱ የተሰጠ ማብራሪያ ነበር፡፡
ጀኔራሉ በመጨረሻም እንዲህ አሉ “ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ኾኖ አለመገኘት ማለት ነው፤ እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ሁሉ ተወጥቻለሁ፡፡ ከጥር 30/1982 ዓ.ም እስከ የካቲት 9/ 1982 ዓ.ም የሞት ሽረት ትግል አደረኩ፡፡ የሻዕቢያን የጥፋት ዓላማ ለመግታት ያላደረኩት ጥረት የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የራሴን ሕይወት በክብር ከማጥፋት እና ለኢትዮጵያ ጀግኖች እና የታሪክ ጸሐፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመኾን ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር እና ዓለም አቀፍ ወደብ በኾነችው ምጽዋ ከተማ እና በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ኾኟለሁ”
የባሕር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ግለሰብ የምትለየው በትንሹ ነው። ይህን የተናገሩበት የስብሰባ ቦታ ከባሕር በሩ ጠረፍ ከ60 ሜትር አይበልጥም፡፡ ይህን እንደተናገሩ በፍጥነት ወደ ጠረፉ አመሩ፡፡ ጀኔራሉ ከምፅዋ ወደብ በስተቀኝ ከሚገኘው ወታደራዊ ወደብ እና መደብር ላይ ደርሰው ጀርባቸውን ለቀይ ባሕር ፊታቸውን ለምፅዋ ሰጥተው ቆሙ፡፡
በፍጥነትም ክላሻቸውን ወደ ባሕሩ ወርውረው ሽጉጣቸውን አውጥተው ራሳቸውን አጠፉ፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ከ150 በላይ የሚኾኑ ወታደሮች መሰል መስዋዕትነትን በዚያች ቅፅበት ለሀገራቸው አበረከቱ፡፡
መቶ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ “አይ ምፅዋ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸውም የዚህን ከፍተኛ የጦር መኮንን ጥረት እና ተጋድሎ፣ ጀብዱ እና ጀግንነት፣ አርቆ አሳቢነት እና ቆራጥነት ይመሰክራሉ፡፡ ጸሐፊው እንደሚሉት የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር አልባ ኾኖ እና እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ እርግጠኛ ኾነው ይናገሩ ነበር ይላሉ፡፡ “የኢትዮጵያ እናቶች ወንድ ልጅ መውለድ እስካለቆሙ ድረስ የባሕር በር ጥያቄ ነገም ቢኾን አይቆምም” እንዳሉም በመጽሐፋቸው ላይ ዋቢ አድርገው አንስተዋል፡፡
የጦር መኮንኑ በዚያ ቀውጢ የጦርነት ወቅት ላይ ኾነውም ስለቀይ ባሕር እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ አጥብቀው ይብሰለሰላሉ፡፡ ያ ሴራ የበዛበት ጦርነት በአሳዛኝ ሁኔታ እያለቀ መኾኑን አውቀውታል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ግን የራሳቸውን እጣ ፋንታ በራሳቸው እንደወሰኑ በልበ ሙሉነት ለሚመሩት ሠራዊት ተናግረዋል። ምናልባትም በሕይወት የሚቆዩት ለሰዓታት ብቻ እንደኾነ እርግጠኛ ናቸው፤ እንዲያም ኾኖ ግን የኢትዮጵያ መጻዒ እጣ ፋንታ እና የባሕር በር አልባ ሀገርነት ያብሰለስላቸው ነበር፡፡
በተጠናቀቀው ጦርነት ዋዜማ ላይ ቆመው ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የኾነው እና ለዘመናት በልጆቿ የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየውን የባሕር በር መዝጋት እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ አይደለም በማለት በምድር ብቻ ተወስና እንድትቆይ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህ ግን የሞት ሞት ነው ይላሉ፡፡ በስተመጨረሻም በሕይወት እና ሞት መካከል ላይ ኾነው የፈለገ ጊዜ ይቆይ እንጂ ጠላት ቀይ ባሕርን እንደያዘ ለዘለዓለም አይኖርም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ይመለሳል የሚል እርግጠኛ ተስፋ ነበራቸው፤ ተስፋቸውንም ለሚወዱት እና ለሚመሩት ሠራዊት በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡
“ያ ተስፋ ዛሬ ነው፤ ያ ትንቢት እውነት ነው” ጀግና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ቆሞ እንኳን የብርሃን ጭላንጭልን የመመልከት እድል አለው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በሞት እና በሕይወት መካከል ባለች ቀጭን መስመር ላይ ቆሞም ስለታሪክ መጨነቅ፣ ስለቀሪ መብሰልሰል፣ ስለመጻዒው ማሰላለሰል እና የሚበጀውን መትለም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት “ስም ከመቃብር በላይ ይውላል” በሚል እሳቤ ምንጊዜም ጽኑ ነው፡፡
ትናንት በርካቶች ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥተው በማንሳታቸው እና በመሞገታቸው ዋጋ ቢከፍሉም ዘመን የባሕር በር ጥያቄን ጉዳይ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ሲያስተጋባ መስማት ግን ምን ያክል አስደሳች እንደኾነ መገመት አይከብድም፡፡ አንድ ትውልድ “ወርቃማ” የሚባለው ኖሮ ስላለፈ ሳይኾን ከባድ የሚባሉ እና ማርሽ ቀያሪ የኾኑ ተግባራትን ከውኖ ሀገርን በኩራት፣ ትውልድን ለተምሳሌነት ማሸጋገር ሲችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና ጥረትም ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉ ትርክትን እና እውነትን ቀያሪ ይኾናል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
            
		