በደብረ ማርቆስ ከተማ የግንባታ ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ ባልገቡ ደንበኞች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።

5
ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ህንፃ ሹም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የግንባታ ፈቃድ መስጠት፣ የግንባታ ክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎችን ጨምሮ ለተጠናቀቁ ግንባታዎች መጠቀሚያ ፈቃድ የመስጠት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሶልያና መሐሪ በበጀት ዓመቱ ያለፈው ሩብ ዓመት በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን መሰረት መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ ከ900 በላይ ተገልጋዮች የፕላን ስምምነት ስለመሰጠቱ ገልጸዋል።
ኀላፊዋ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ እና በነባር ለ981 ደንበኞች የግንባታ ፈቃድ መስጠት ተችሏል።
ባለፈው ሩብ ዓመት ከ900 በላይ ግንባታዎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መሠራታቸውንም የተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዋ አመላክተዋል። ለተጠናቀቁ ግንባታዎች የመጠቀሚያ ፈቃድ ከመስጠት አኳያ ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
የግንባታ ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ ባልገቡ ደንበኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል። የፕላን ስምምነት ወስደው ወደ ቀጣይ ተግባራት ባልገቡ 23 ደንበኞች እንዲሁም የግንባታ ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ ባልገቡ 28 ደንበኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡
ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ግንባታ የሚገነቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ኀላፊዋ ግንባታቸው ተጀምሮ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ግንባታዎች በፍጥነት እንዲጠናቁቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article‎ለማር ምርት ጥራት ይጠነቀቃሉ ?
Next article“ያ ተስፋ ዛሬ ነው፤ ያ ትንቢት እውነት ነው”