የኮምፒዩተር ወንጀል ምንድን ነው?

6
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሳይበር ጥቃት ኾን ተብሎ ያልተፈቀዱ የኮምፒውተር ሥርዓቶችን፣ መሠረተ ልማቶች እና ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ ዳታዎችን መበዝበዝ እና አገልግሎት የማስተጓጎል ተግባር ነው።
የሳይበር ጥቃት ከቴክኖሎጅ መሥፋፋት ጋር እያደገ የመጣ፣ የሀገራትን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ ሰላም እና ደኅንነትን የሚነሳ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በቀላሉ የሚዳረስ አደገኛ ወንጀል ነው።
የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ አማራጮችን መጠቀም የግድ ይላል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (INSA) ዋና ዳይሬክተር የሕግ እና የፖሊሲ ጉዳዩች አማካሪ ፍቅረሥላሴ ጌታቸው እንዳብራሩት የሳይበር ደኅንነት በሳይበር ምኅዳሩ የሚያጋጥሙ የደኅንነት ተጋላጭነቶችን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን፣ የአሠራር ሥርዓቶችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ያጠቃልላል።
በኢትዮጵያም የሳይበር ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው በሥራ ላይ መዋላቸውን ይናገራሉ። ከእነዚህም ውስጥ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ዓ.ም አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
በአዋጁ እንደተቀመጠው የኮምፒዩተር ወንጀል ማለት በኮምፒዩተር ሥርዓት እና በኮምፒዩተር መረጃ ወይም ኔትዎርክ ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ያጠቃልላል።
በቴክኖሎጅ ውጤቶች እና በኔትወርክ አማካይነት የኮምፒዩተር ዳታን ከመደበኛ አሠራሩ ውጭ ማበላሸት ማዛባት እና ማሠራጨት የኮምፒዩተር ወንጀል አካል እንደኾነም ነው አቶ ፍቅረስላሴ ያብራሩት።
የአንድን ሰው ወይም ተቋም ኮምፒዩተር ሳይፈቀድለት ማግኘት በሕግ የተከለከለ እና የሚያስጠይቅ መኾኑንም አስረድተዋል።
ኾነ ብሎ ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ የኮምፒዩተር ሥርዓት፣ የኮምፒዩተር ዳታ ወይም የኔትዎርክ ተደራሽነት በከፊልም ኾነ በሙሉ ማግኘት ወንጀል እንደኾነ አንስተዋል፡፡ የኮምፒዩተር ወንጀል ሲፈጸም ከቀላል እስከ ከባድ የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል በአዋጁ የተደነገገ መኾኑንም ነው አቶ ፍቅረሥላሴ የገለጹት።
በአዋጁ እንደተገለጸው፦
👉 ማንኛውም ሰው ኾነ ብሎ ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ የኮምፒዩተር ሥርዓት፣ የኮምፒዩተር ዳታ ወይም ኔትዎርክ በከፊልም ሆነ በሙሉ ያገኘ እንደኾነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 50 ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚጠየቅ በአዋጁ ላይ ተመላክቷል፡፡
👉 ወንጀሉ የተፈጸመው በቁልፍ የመሠረተ ልማት ላይ ከኾነ ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣም ተደንግጓል፡፡
👉 የሌላን ሰው ክብር ወይም መልካም ስም የሚያጎድፍ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ስዕል ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካኝነት ያሠራጨ እስከ ሦስት ዓመት ቀላል እሥራት ወይም ከብር 30 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚያስቀጣ ተቀምጧል፡፡
👉 ያለ ፈቃድ ወይም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ ይፋዊ ያልኾነን የኮምፒዩተር ዳታ ወይም የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት የጠለፈ ከ5 ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ 50 ሺህ በሚደርስ ቅጣት ያስቀጣል፡፡
👉 የኮምፒዩተር ጠለፋ ወንጀሉ በቁልፍ መሠረተ ልማት ላይ የተፈጸመ ከኾነ ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 100 ሺህ እስከ ብር 200 ሺህ እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተገልጿል፡፡
👉 ኾነ ብሎ ያለ ፈቃድ ወይም ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ የኮምፒዩተር ዳታን በማስገባት፣ በማሠራጨት፣ በማጥፋት ወይም በመለወጥ የኮምፒዩተር ሥርዓትን ወይም ኔትወርክን መደበኛ ተግባር በከፊልም ኾነ ሙሉ በሙሉ ያደናቀፈ፣ ያወከ፣ ያወደመ ወይም እንዲቋረጥ ያደረገ ከሦስት ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ በማይበልጥ ቅጣት ያስቀጣል ይላል ሕጉ።
👉 ለአካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ ወሲባዊ ድርጊት በግልጽ ሲፈጸም የሚያሳይ፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ ፖስተር፣ ቪዲዮ ወይም ምስል ኾነ ብሎ ያዘጋጀ፣ ያሠራጨ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያከፋፈለ፣ ሌሎች እንዲያገኙት ያመቻቸ ወይም ያለ ፈቃድ ይዞ የተገኘ ከሦስት ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።
👉 ለወታደራዊ ጥቅም ወይም ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ሲባል ጥብቅ ምስጢር ተብሎ በተሰየመ የኮምፒዩተር ዳታ ወይም ዳታው በሚገኝበት የኮምፒዩተር ሥርዓት ወይም ኔትዎርክ ላይ የተፈጸመ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት የተፈጸመ የኮምፒዩተር ወንጀል ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተመላክቷል፡፡
ኮምፒዩተሮችን በምስጢር መቆለፍ፣ ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፣ ይለፍ ቃልን በየወቅቱ ማደስ፣ የስልክ እና የኮምፒዩተር መተግበሪያዎችን አፕዴት ማድረግ፣ ያልታወቁ ሊንኮችን አለመክፈት፣ የመረጃ መቅጃ ወይም ባክ አፕ መያዝ፣ አንቲቫይረስ መጠቀም የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚወሰዱ የጥንቃቄ መንገዶች መኾናቸውን አቶ ፍቅረሥላሴ አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next article‎ለማር ምርት ጥራት ይጠነቀቃሉ ?