
ጎንደር: ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ አስታውቋል።
ወጣት አደም ደሳለኝ የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ነው። በ2017 በጀት ዓመት በወተት እና የወተት ውጤቶች ላይ በማኅበር ተደራጅቶ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ውጤታማ ለመኾን ጥረት እያደረገ መኾኑን ተናግሯል።
ሌላኛው ከጓደኞቹ ጋር በዶሮ ልማት ሥራ ላይ የተሠማራው ዳውድ ሙሐሙድ ከ200 በላይ ዶሮዎች ቀርበውላቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሷል። በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ደስተኛ እንደኾነም ገልጿል።
ወጣቶቹ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመኾናቸው በፊት በቀን ሥራ እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ሢሠሩ እንደነበር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ልዑል መስፍን በ2017 በጀት ዓመት 6 ሺህ 70 ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው አስታውሰዋል።
ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ 12 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል። ሼዶችን በመገንባት መሥሪያ ቦታ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለ5 ሺህ 800 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና 18 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ለመስጠት እንደታቀደም ተናግረዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች የብድር አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደገፋው ታከለ በሰሜን ጎንደር ዞን ባለፈው በጀት ዓመት 36 ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ ለ37 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
የሥራ ፈላጊ ልየታ እና በዘመናዊ መሣሪያ የተደገፈ ምዝገባ እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከ13 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊዎች በዞኑ ተመዝግበዋል ብለዋል። ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች የብድር አቅርቦት ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል።
የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		