ያለበቂ ምክንያት በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል።

6
ደብረታቦር: ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ መክንያቶች የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የሚመለከታቸው ሁሉ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኛ እንደኾኑ ለአሚኮ የተናገሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ ሙላው አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር የዋጋ ንረት እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ሰበብ የዋጋ ንረት እንዳይኖር የንግድ ባለሙያዎች እና ማኅበረሰቡ ተደጋግፈው መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛዋ ሃሳባቸውን ለአሚኮ ያጋሩት የመንግሥት ሠራተኛ ወይዘሮ እንደሻሽ መኮነን በዘይት እና በሌሎች ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ሸማች ማኅበራት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሲመለከት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ነው ያሉት።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት
መምሪያ ኀላፊ ቢኒያም ባየ ገበያውን ለማረጋጋት የጤፍ ምርት ለመንግሥት ሠራተኞች በዝቅተኛ ዋጋ መቅረቡን ተናግረዋል።
በቀጣይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት ምርቶችን ለማቅረብ እንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ያለበቂ ምክንያት በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በንግድ ሥርዓቱ ላይ እክል በሚፈጥሩት እና ሕግን በሚተላለፉት ላይ ደግሞ እርምት እንደሚወሰድም ነው ያስገነዘቡት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየጠራ አቋም በመያዝ ባንዳዎችን እና ባዕዳዎችን መመከት ይገባል።
Next articleየሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።