
ባሕር ዳር: ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የውጭ ባዕዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት አናጋው መድረኩ የከተማ አሥተዳደሩ የጸጥታ መዋቅር በሀገራዊ እና በክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የሚያስችል ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና የከተማ አሥተዳደሩን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሰላምና ጸጥታ ኹኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም አቶ ጌትነት ገልጸዋል። በተሠራው ሥራም መሠረታዊ ለውጦች መኖራቸውን አንስተዋል።
የተገኘው ሰላም ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ በመሠራቱ መኾኑን ነው ያመላከቱት።
በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚመለከታቸው ተቋማትም ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ የጸጥታ አካላት የተጣለባቸውን ኀላፊነት በሙያዊ ዲሲፕሊን ሕዝብን ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሕዝቡም በመደራጀት፣ አካባቢውን በመጠበቅ እና መረጃ በመሥጠት በኩልም ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የኾኑት ዋና ኢንስፔክተር ገብረ ዮሐንስ ኪዴ ወንጀልን ለመከላከል ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ ሥራ በመሥራት ከገባንበት የጸጥታ ችግር ለመውጣት ወሳኝ ነው ብለዋል።
መድረኩ በሀገራዊ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስላለንበት ነባራዊ ኹኔታ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ በትኩረት ለመሥራት ያግዛል ነው ያሉት።
ለዚህም በውጭ እና በውስጥ ሀገራችንንም ኾነ ክልሉን የሚረብሹ የውስጥ እና የውጭ ኀይሎችን ለመታገል ቁርጠኛ መኾን እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ዋና ኢንስፔክተር ሁሉንአየሁ ዓለም በባሕር ዳር ከተማ ጸጥታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማኅበረሰቡ የራሱ አድርጎ መውሰድ እና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የተጀመሩት የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን መሰለፍ ይገባል ነው ያሉት።
የጸጥታ ኀይሉ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታውን ተረድቶ የጠራ አቋም በመያዝ ባንዳዎችን እና ባዕዳዎችን መታገል እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		