
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ውል አሠራር ግብርናውን ለማዘመን ከሚረዱ ሥልቶች አንዱ ነው። የግብርና ምርት ውል በአምራቹ እና በአስመራቹ መካከል የሚደረግ የሥምምነት ሰነድ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የግብርና ምርቶች አመራረት እና ግብይት ላይ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ አስቀድመው ይዋዋላሉ።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው የግብርና ምርት ውል ተሞክሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ረዥም እድሜ ያስቆጠረ አሠራር ነው።
በቻይና ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየተሠራበት ይገኛል። ሕንድ ደግሞ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደ ጥጥ፣ ትምባሆ፣ ሸንኮራ አገዳ እና የንግድ ሰብሎችን በዘመናዊ የግብርና ውል አሠራር በስፋት በማምረት ትታወቃለች።
ቬትናም በግብርና አሠራር የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ብሎም ግብርናን ለማዘመን ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። በጎረቤት ሀገር ኬኒያም በርካታ አርሶ አደሮች በግብርና ምርት ውል ተሠማርተው ተጠቃሚ እየኾኑ ነው።
በሀገሪቱ 50 በመቶ የሻይ፣ 60 በመቶ፣ የሸንኮራ አገዳ እና መቶ በመቶ የጥጥ ልማት በግብርና ውል እርሻ ልማት የተሸፈነ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት ሥራ አሥፈጻሚ ደረጀ አበበ እንደገለጹት የግብርና ምርት ውል በኢትዮጵያ ከ1942 ዓ.ም ጀምሮ በስኳር አገዳ፣ በሻይ ቅጠል እና ጥጥ ምርቶች ላይ ሲተገበር ቆይቷል።
የወንጂ ስኳር ፋብሪካ እስካሁንም በትግበራ ላይ ይገኛል። በዚህ ወቅትም ግብር ሚኒስቴር ከሚሠራቸው አራት የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ውስጥ አንዱ የግብርና ምርት ውል መኾኑን ነው የገለጹት።
በተለይም ደግሞ በእንስሳት ዘርፍ በጥሬ ወተት ማሠባሠብ፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ እና በሥጋ ምርት፣ በሰብል ደግሞ በእህል ምርት፣ በምርጥ ዘር ማምረት፣ በቢራ ገብስ ልማት፣ በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተር እና መሰል ምርቶች ላይ እየተሠራበት ይገኛል። በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ደግሞ ሮዝመሪ፣ አቮካዶ፣ ቡና እና ሻይ ልማት ይጠቀሳሉ።
ሥራ አሥፈጻሚው እንዳሉት በግብርና ምርት ውል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የግብርና ውል አዋጅን በማጽደቅ ወደ ሥራ ተገብቷል። የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያም ተግባራዊ ተደርጓል።
የውል ስምምነቱ የአምራቹን እና የአስመራቹን ሙሉ ስም እና አድራሻ፣ የውሉን ዓላማ፣ የማሳውን ቦታ ስፋት እና አዋሳኝ የያዘ ነው። የአምራቹን እና የአስመራቹን መብት እና ግዴታዎች፣ የምርት ዓይነት እና የጥራት መስፈርቶችንም ያካተተ ነው።
የመግዣ ዋጋ እና የክፍያ አፈጻጸም ሁኔታን፣ ለአምራቹ የሚቀርቡ የድጋፍ አይነቶችን፣ የውል ቆይታ ጊዜ እና መሰል ነጥቦችንም ያካተተ መኾኑ ተገልጿል።
የግብርና ምርት ውል ለአምራቹ፣ አስመራቹ፣ ማኅበረሰብ እና ለመንግሥት ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል?
ለአምራቾች እንደ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ኬሚካል፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት መሠብሠቢያ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያደርጋል። የኤክስቴንሽን፣ የሥልጠና፣ የምክር ድጋፎች እንዲያገኙም ዕድል ይፈጥራል።
አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው ገበያ እንዲኖር፣ የምርት ማጓጓዥያ ትራንስፖርት ማመቻቸት፣ የአምራቹን አሠራር በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል።
ለአስመራቹ ደግሞ ጥራቱን የጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው የምርት አቅርቦት እንዲያገኝ ያደርጋል። የመሬት እጥረት ችግርን ያቃልላል፣ አምራቹ በአስመራቹ አሠራር ላይ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል። ሰላማዊ እና ዘለቄታ ያለው ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ ያስችላል።
የአካባቢውን ማኅበረሰብም በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ተጠቃሚ ያደርጋል። መንግሥትም በግብዓት አቅርቦት እና በኤክስቴንሽን ድጋፍ ያለበትን ጫና ይቀንስለታል፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠርም ያደርጋል፤ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ይቀንሳል፣ የኤክስፖርት ምርት አቅርቦትንም ለማሳደግ አቅም ይፈጥራል።
አሠራሩ በአማራ ክልልም ከተተገበረ ዓመታትን አሥቆጥሯል። በ2017/18 የምርት ዘመን እንኳ ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በውል እርሻ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረቱ ይገኛሉ።
በውል እርሻ እየተሳተፉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ውስጥ አርሶ አደር ይርሳው በሪሁን ይገኙበታል። አርሶ አደር ይርሳው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ በቦሎቄ እና አኩሪ አተር ውል ወስደው እያመረቱ ይገኛሉ።
በውል እርሻ በመሳተፋቸው ዘር፣ ማዳበሪያ እና ኬሚካል በወቅቱ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ይህም ማሳቸውን በወቅቱ በዘር አንዲሸፍኑ፣ ከተዘራ በኋላም በወቅቱ ማሳውን እንዲንከባከቡ፣ እንዲሠበሠብ እና ጥራት ያለው ምርት በወቅቱ እንዲያቀርቡም ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
አርሶ አደሩ እንዳሉት በ2017/18 የምርት ዘመን 60 ሄክታር መሬት በቦሎቄ እና አኩሪ አተር በግብርና ውል እርሻ አልምተዋል። በዚህም አኩሪ አተር በሄክታር እስከ 30 ኩንታል፣ ቦሎቄ ደግሞ እስከ 25 ኩንታል እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
በቀጣይ ከዚህ በተሻለ መንገድ ለማምረት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይ አምራቹ ጥራት ያለውን ምርት እንዲያመርት፣ አስመራቹ ደግሞ የተመረተውን ምርት እንዲረከብ የሚያስገድድ መመሪያ መውጣቱ ሁለቱ ተዋናዮች ተቀራርበው እንዲሠሩ አቅም የሚፈጥር እና ከዚህ በፊት የነበረውን የገበያ ችግርም የሚፈታ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው እንዳሉት አሁን ላይ በ10 ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ በመሳሰሉ ሰባት ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
631 አስመራቾች እየሠሩም ይገኛሉ። ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ውል ወስደው እያመረቱ መኾኑንም ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ በክልሉ ከ783 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በውል እርሻ መልማቱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ከዚህም 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን ገልጸዋል።
ይህም የምግብ ፍጆታን ለማረጋገጥ፣ ለኤክስፖርት እና ለኢንዳስትሪ ግብዓት ለማቅረብ አቅም እንደሚኾን ገልጸዋል። በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች በሁሉም የሰብል ዓይነቶች፣ በእንስሳት ሃብት እና ፍራፍሬ ላይ ለመሥራት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአምራቾች እና አስመራቾች መካከል ሥምምነት ከተደረሰ በኋላ በሁለቱም በኩል ውላቸውን ያለማክበር ችግሮች እንደነበሩ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ አስመራቾች ያስመረቱትን ውል በውላቸው መሠረት ስለማይገዙ አምራቾች ለኪሳራ ሲዳረጉ መቆየታቸውን ነው የገለጹት። አሁን ላይ ግን አስመራቾች ያስመረቱትን ምርት በውሉ መሠረት እንዲረከቡ የሚያስችል አስገዳጅ ሕግ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል። በውሉ መሠረት ተግባራዊ የማያደርጉ አካላት ደግሞ ተጠያቂ ይኾናሉ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		