
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የዱር እንሰሳት መርሐግብር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ከ38 በላይ ሀገራት የመጡ ፖሊሲ አውጭዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ ኢትዮጵያ የሰው ዘር እና የቡና መገኛ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ባሕሎች እና ቅርሶች ባለቤት መኾኗን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለቱሪዝም እና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ምቹ መኾኑን ያሰኑት ድኤታ
ይህንኑ ጸጋ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ለብዝኀ ሕይወት እና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።
ጉባኤው በዱር እንሰሳ ጥበቃ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት እና በዘርፉ ያለው ትብብር የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚኾንም አንስተዋል።
የዓለም አቀፉ የዱር እንሰሳት መርሐግብር ከፍተኛ ባለሙያ ሃና ፌርባክ መርሐግብሩ ከ30 በላይ ሀገራት ላይ ከዱር እንሰሳት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የዱር እንሰሳት በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይጠፉ፣ እንዳይሰደዱ የሚደረገው ጥበቃ እና እንክብካቤ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ ሱዳን እና የደቡብ ሱዳን የኦፕሬሽን ሥራ አሥኪያጅ ጁሊያና ቪክቶር ለዱር እንሰሳት ተገቢውን ጥበቃ የሚያደርጉ ሀገራት ከቱሪዝም ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።
ይሁን እና በዱር እንሰሳት ላይ የመጥፋት አደጋ መጋረጡን ጠቅሰዋል። በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች የዱር እንሰሳት ከአካባቢያቸው እንዲሰደዱ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።
ሀገራት ከዱር እንሰሳት ሃብታቸው ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በቅንጅት እና በትብብር እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም አቀፉ የእንሰሳት መርሐግብር ዓመታዊ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ የወጣው መርሐግብር ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		