“በክብር የነገሡት፤ በግርማ የታጀቡት”

18
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአበው ሥርዓት በግርማ ነግሠዋል፤ በአበው ሕግ ተገዝተዋል፤ ሀገራቸውን ያገለግሉ ዘንድ በሕያው አምላክ ፊት ቃል ኪዳን ገብተዋል፤ ቃል ኪዳናቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ታትረዋል።
ከአበው የተቀበሏት፤ በዓምላክ ፈቃድ ዙፋን ተቀምጠው የሚመሯት፤ በበትረ መንግሥታቸው መንገዷን የሚጠርጉላት ሀገራቸው ከፍ ከፍ ትል ዘንድ ሠርተዋል።
ተናግረው ይሰማሉ፤ መክረው ይመልሳሉ፤ ገስጸው ያስተካክላሉ፤ ዘምተው ያሸንፋሉ፤ አስበው ያደርጋሉ፤ ጀምረው አምላካቸውን ይዘው ይፈጽማሉ።
አበው ስለ ጠበቋት ሀገራቸው በጽናት ቆመዋል፤ ከአበው ስለተቀበሏት የከበረችው ሠንደቅ ዓላማቸው በጀግንነት ተፋልመዋል፤ ነጻነቷን እንዳታጣ ከጠላቶቿ ጋር ተጋጥመዋል፤ ዓለም ሁሉ ፊቱን ባዞረባቸው ጊዜ እውነትን፣ ቃል ኪዳንን እና ተስፋን ይዘው ብቻቸውን ቆመዋል።
ሃሰተኞች በሚፈርዱበት፣ ሀሰተኞች በሚመሰክሩበት፣ ሀሰተኞች የፍርዱን ውሳኔ በሚያጸኑበት፣ የፍርድ ሚዛን ሁሉ ወደ ቅኝ ገዢዎች በምታዘነብልበት በዚያ ጊዜ በተስፋ ቆመዋል፤ ከእውነት ጋር ቆመው የእውነት፣ በእውነት፣ ስለ እውነት ለሀገራቸው ነጻነት ታግለዋል።
እውነትን ይዘው ሀሰተኞችን በፍርድ ዓደባባይ አሸንፈዋል፤ ቅኝ ገዢዎችም በጦር ሜዳ ድል መትተዋል፤ በድል አድራጊነትም በግርማ እና በከፍታ በዓደባባይ ታይተዋል፤ በዙፋን ላይ እንደ ጫካ አንበሳ በአስፈሪ ክብር ተቀምጠዋል ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ።
በቅኝ ገዢዎች የተበተኑትን ሰብስበዋል፤ መለያየትን አውግዘው አንድነትን አምጥተዋል፤ የአንድነቱን መሠረት አጥብቀዋል፤ የተረሱትን አስታውሰዋል፤ አንገታቸውን የደፉትን ቀና እንዲሉ አድርገዋል፤ የተገፉትን ደግፈዋል፤ ስለ ራሳቸው በራሳቸው የማይመክሩትን ስለ ራሳቸው እንዲመክሩ፣ መፍትሔም እንዲያበጁ አድርገዋል።
በቅኝ ገዢዎች የተበተኑትን በአንድነት ሰብስበው አቅማቸውን አደርጅተዋል፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲናገሩ መንገዱን አሳይተዋል፤ ስለ እነርሱ ከእነርሱ በላይ እንደሌለ አሳይተዋቸዋል፤ በቅኝ ገዢዎች ምክንያት የጨለመችባቸውን የነጻነት ጀንበር እንዲመለከቱ አድርገዋል፤ በነጻነት ጀንበር በብርሃን ይመላለሱ ዘንድ አድርገዋል ጃንሆይ።
እኒህ አያሌ ታሪክ የሚነገርላቸው፤ አፍሪካውያን የአንድነታችን አባት የሚሏቸው ንጉሠ ነገሥት ዘውድ የጫኑት፣ በከበረው ዙፋን ላይ የተቀመጡት፣ በትረ መንግሥቱን የጨበጡት፤ ቅብዓ መንግሥቱን የተቀቡት፤ የአበውን አደራ ይሸከሙ ዘንድ እጃቸውን ከፍ አድርገው ቃል ኪዳን የገቡት በዛሬዋ ቀን ነበር፤ ጥቅምት 23/1923 ዓ.ም።
የነገሡበት ቀን በሃያ ሦስት፣ የነገሡበት ዓመተ ምኅረት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ ሦስት፣ የነገሡበት ደብርም ክብረ በዓሉ የሚከበረው በሃያ ሦስት ነው። ሃያ ሦስት የተገጣጠመላቸው ባለ ግርማው ንጉሥ።
ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሕይዎቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ንግሥናቸው ሲጽፉ መስከረም 17/1909 ዓ.ም ንግሥት ዘውዲቱ ሲነግሡ እኔም ለአልጋ ወራሽነቱ እና ለእንደራሴነቱ ስለተመረጥሁ በባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴነቴ የመንግሥቱን ሥራ እየሠራሁ 14 ዓመታት ቆየሁ።
ንግሥት ዘውዲቱ መጋቢት 24/1922 ዓ.ም ስላረፉ በማግሥቱ የንጉሠ ነገሥቱ ዐዋጅ ተነግሮ በዙፋኑ ተቀመጥሁ።
ወደ ፊት ያለው ወራቱ ክረምት ስለነበረ የዘውድ በዓላችን ሰባት ወራት እንዲቆይ አደረግን። በኢትዮጵያ ያሉ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ፣ ባላባቶችም ሁሉ፣ በየገዳማቱ ያሉ አባቶች፣ የየአድባራቱ አለቆች፣ መጥተው የደስታችን ተካፋዮች እንዲኾኑ የጥሪ ደብዳቤ ተላከላቸው። ለዘውድ በዓሉም ዝግጅት ተደረገ ብለዋል።
ልብሠ መንግሥቱ፣ ዘውዱ እና ሉሉ፣ በትረ መንግሥቱ እና ሰይፉ፣ ቀለበቱ ይህንም የመሰለው ሁሉ በተለየ በወርቅ እና በአልማዝ እየኾነ ተሠራ። ለመሳፍንቱ፣ ለመኳንንቱ፣ ለጦር አበጋዞች ሁሉ እንደየ ክብራቸው የክብር ልብስ ተዘጋጀላቸው።
በዘውድ በዓሉ ዋዜማ በጅሮንዱ የንጉሠ ነገሥቱን ልብሰ መንግሥት እና ዘውዱን፣ ሉሉን፣ በትረ መንግሥቱን፣ ሰይፉን፣ የአልማዝ ቀለበቱን፣ የእቴጌይቱንም ልበሰ መንግሥት እና ዘውድ፣ የአልማዝ ቀለበት በሠረገላ አስገብቶ በታላቅ ሰልፍ ወስዶ በመናገሻው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለሊቀ ጳጳሳቱ አስረክቦ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸለይበት አደረ ይላሉ።
ንጉሠ ነገሥቱ እና እቴጌይቱ በሌሊት ወደ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አቀኑ። ጸሎቱም ማካሄዱን ቀጠለ።
ጃንሆይ ሲጽፉ ሥርዓተ ንግሡ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሊቀ ጳጳሳቱ አቡ ቄርሎስ ገበታው የወርቅ የኾነ ወንጌል ይዘው ቀርበው የመሐላ ቃል እንድንፈጽም አደረጉ ብለዋል።
ብላቴ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተሰኘው መጽሐፋቸው ሲጽፉ የዘውዱ ዋና በዓል ጥቅምት 23/1923 ዓ.ም እሑድ ነበር። ቅዳሜ ማታ የመናገሻ ጊዮርጊስ ካህናት እና ከየአድባራቱ ተመርጠው የመጡ መዘምራን ከማታው ጀምረው ማኅሌት ቆመው አደሩ።
እኩሌቶቹ መወድስ ሲቆሙ እኩሌቶቹ ክስተት አርያም ያደርሱ ነበር እና ማኅሌቱ ደምቆ አደረ።
ንጉሠ ነገሥቱ እና እቴጌይቱም በሌሊት በመሳፍንቱ እና በመኳንንቱ ታጅበው ወደ ቤተክርስቲያን መጥተው ለዚህ ማዕረግ ላበቃቸው ከዚህ ዕለት ላደረሳቸው አምላክ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ወደ ማረፊያ ድንኳን ሄደው ጸሎተ ሕሊና ሲያደርሱ አደሩ።
ጠዋት ሲነጋ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ ሙሉ የማዕረግ ልብሳቸውን ከኒሻን ጋር ለብሰው የራስ ሉል እና የራስ ወርቅ ደፍተው በአዳራሹ ውስጥ በተሰናዳላቸው ስፍራ በየማዕረጋቸው ተቀመጡ። ጳጳሳት እና መምህራን ለሥርዓቱ ተዘጋጁ።
ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ ንግሥ ወደሚፈጸምበት ገቡ። በመንበሩ አጠገብ ተሳልመው ጸሎት አደረሱ። ጸሎታቸው እንደጨረሱ በተሰናዳው ዙፋን ላይ ተቀመጡ።
በዚህም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ አቡነ ቄርሎስ ፊታቸውን ወደ መሳፍንቱ እና ወደ መኳንንቱ አዙረው እንዲህ አሉ።
“እናንት የኢትዮጵያ መሳፍንት እና መኳንንት፣ የጦር አለቆች ወታደሮች እና ሠራዊቶች፣ በቤተ ክህነትም ያላችሁ ሊቃውንት እና አለቆች መምህራን እና ቀሳውስት ሁሉ ንጉሠ ነገሥታችን ግርማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሰሎሞን እና ከንግሥተ ሳባ ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ ሳይቋረጥ ከመጣው መኾኑን ታውቃላችሁ።
አሁን በእግዚአብሔር ፈቃድ እና ቸርነት ዘውድ ጭኖ እንዲነግሥ ልቀባው ነው እና በሥጋዊ እና መንፈሳዊ ሥራው ሁሉ ሀገርም በማሠልጠን ሃይማኖትም በማጽናት በዘመኑም ኢትዮጵያ በዕውቀት እና በትምህርት በጥበብም ከፍ ከፍ እንድትል በመትጋት ከወሰን እስከ ወንሰን የኢትዮጵያ ባንዲራ እንዲዘረጋ በማድረግ ይህንንም በመሰለው በመልካም ሥራው ሁሉ እንድትገዙለት እና እንድትረዱት አደራ እላችኋለሁ” አሉ።
ሕዝቡም በዕልልታ አጀባቸው።
ከዚያም ልብሰ መንግሥቱን አለበሷቸው፤ ቤተ መንግሥቱን አስጨበጧቸው፤ ሉሉንም ሰጧቸው፤ የአልማዙን ቀለበቱንም አጠለቁላቸው፤ የንግሥና ወግ እና ማዕረግ የኾነው ሰይፉን እና ጦሩንም ሰጧቸው፤ ቅብዓ መንግሥቱንም ቀቧቸው፤ ዘውዱንም ባርከው ደፉላቸው፤ በዚህም ጊዜ እልልታው አስተገባ፤ ታላቅ ደስታም ኾነ።
ንጉሡም በግርማ ኾነው ከዙፋናቸው ላይ ተቀመጡ። የእተጌዋም በሥርዓቱ መሠረት ተፈጸመ። የአልጋ ወራሹም ከዙፋኑ ግርጌ ኾነው ቃል ኪዳን አሠሩ። እልልታውና ጭብጨው ከዳር እስከ ዳር አስተጋባ። ንጉሡና እና ንግሥቷ ከፍ ባለ ሥፍራ ኾነው በታዩ ጊዜ እልልታው ቀለጠ።
በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የተፈጸመው ሥርዓት በተጠናቀቀ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱና እቴጌይቱ በስድስት ፈረሶች በሚሳብ በወርቅ ሠረገላ ተቀምጠው፣ ከፊትም ከኋላም በመሳፍንት እና በመኳንንት ታጅበው፣ በሠራዊት ሰልፍ መካከል አልፈው ወደ ቤተ መንግሥታቸው ተመለሱ።
መሳፍንት እና መኳንንት የመንግሥታት መልእክተኞችም በየማዕረጋቸው በሠረገላ እና በአውቶሞቢል ኾነው አጀቡ። እምቢልታውና መለከቱ ሲንካለል፣ ነጋሪቱ እየተጎሰመ ገብር ገብር ሲል እጅግ ደስ ያሰኝ ነበር።
በመንገድ ዳር ኾኖ ለማየት የተሰበሰበውም ሕዝብ ሰላምታ እየሰጠና እጅ እየነሳ ሺህ ዓመት ያንግሥዎ እያለ አጨበጨበ። ከቤተ መንግሥት በደረሱ ጊዜም ንጉሠ ነገሥቱ እና እቴጌይቱ ለመሰናበቻ በተሰናዳው ሥፍራ ቆመው ሲያዩት ሕዝቡ ሁሉ እንደገና እያጨበጨበ ሺህ ዓመት ያንግሥዎ እያለ እየመረቀ ተሰናበተ። የዘውዱ በዓል ግብርም ተገባ ተብሎ ተመዝግቧል።
አምባሳደር ዘወዴ ረታ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት በተሰኘው መጽሐፋቸው ንጉሠ ነገሥቱ እና ንግሥቲቱ በወርቅ ሰረገላ ኾነው ወደ ቤተ መንግሥታቸው ሲያመሩ ከሕዝቡ የጎረፈላቸው የደስታ መግለጫ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው እየተባለ ይነገራል ብለው ጽፈዋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እስከ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ድረስ በተደረገው የአንድ ሰዓት የእርጋታ ጉዞ ላይ እምቢልታው እና መለከቱ ሲነፋ፣ ነጋሪቱ ሲጎሸም፣ ካህናቱ ሲዘምሩ፣ ወታደሩ ሲሸልል፣ ከዚህ ሁሉ ጋር የሴቶች እልዕልታ እና የወንዱ ጭብጨባ ሲያስተጋባ፣ የአዲስ አበባን የጥቅምት ፀሐይ እጅግ ያጋላው ይመስል ነበር።
በዋዜማው ቅዳሜ ከማታው በአራት ሰዓት የተጀመረው ጸሎተ ቅዳሴ እና የንግሥ በዓል ሥርዓት የተፈጸመው በማግሥቱ እሑድ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲኾን ነው።
ለአሥራ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሠ ነገሥቱ እና ንግሥቲቱ ያሳዩትን ጥንካሬ እና የመንፈስ ጽናት ያላደነቀ አልነበረም።
በተለይም በበዓሉ ተካፋይ ለመኾን ከአውሮፓ፣ ከእስያ እና ከአሜሪካ የመጡት የአሥራ አንድ ሀገራት እንደራሴዎች ከዚህ ቀደም በየትኛውም ዓለም ያላዩትን ይህን እጅግ ረጅም እና ከፍተኛ የኾነ ሥነ ሥርዓት ሲመለከቱ ኢትዮጵያ ያላት ጥንታዊ ባሕል ምን ያህል የሚደንቅ እና የሚከበር መኾኑን መገንዘብ የሚያስችላቸው ነው ብለው ጽፈዋል።
ዘውድ በጫኑበት ዕለት በእርስዎ መሪነት ኢትዮጵያ ዘመናችን ያፈለቀውን ሥልጣኔ አግኝታ በዓለም ላይ የክብር ቦታ እንድትይዝ የሚያደርጉት ጥረት የተባረከ ይኹን ተብለው እንደተመረቁ ሁሉ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ በነጻነት የተቀበሏት ሀገራቸውን ታላቅ እና ገናና ትኾን ዘንድ አቅማቸው የፈቀደውን ሳይሰስቱ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን ክብር እና ጥቅም አስከብረዋል፤ ገናናቷን በአፍሪካ እና በቀረው ዓለም ደጋግመው አስመስክረዋል። የአፍሪካውያንን የአንድነት መሠረት ጥለው አልፈዋል።
ኢትዮጵያን ስላገለገሉ እናመሰግንዎታለን፤ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር ስለታተሩ እናከብረዋታል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየታሪክ መዳረሻችን እና የሕልውና መሠረታችን ቀይ ባሕር እና ዓባይ ነው።