የታሪክ መዳረሻችን እና የሕልውና መሠረታችን ቀይ ባሕር እና ዓባይ ነው።

17
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ እንደኾኑ የሚነገርላቸው የዳማት እና የአክሱም ስራወ መንግሥታት ሥልጣኔያቸው የቀይ ባሕር በርን ተከትሎ የተመሠረቱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የአክሱም ዘመነ መንግሥት በመሀል ሀገር በተነሳው የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ መውደቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት አድርጓል።
የኢትዮጵያ የኃያልነት ዘመን የነበረው የአክሱም ሥራወ መንግሥት ማክተማሚያ እና የዛጉዬ ሥራወ መንግሥት መባቻም ኤርትራ የምትባል ሀገር ፈጽሞ አልነበረችም። ኤርትራ እንደ ሀገር በጣሊያን ቅኝ ግዛት ዘመን የተከሰተች ሀገር መኾኗን የታሪክ መዛግብት አስረግጠው ይመሰክራሉ።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር ያላነስ የባሕር ክልል ነበራት። ኢትዮጵያ ከአሰብ እስከ ምጽዋ፣ ከዘይላ እሰከ ታጁራ፣ ከአዶሊስ እሰከ በርበራ ድረስ ያሉ ጥንታዊ ወደቦችን በባለቤትነት እና በበላይነት ለዘመናት ስታሥተዳድራቸው እና ስትገለገልባቸው እንደነበር ታሪክ የሚዘክረው ትውልድ የማይረሰው ሀቅ ነው።
በእርግጥም ቀይ ባሕር በኢትዮጵያ የታሪክ ገጽ ባለብዙ መልክ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ሌፍተናንት ኮማንደር መረባ አቶምሳ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ምሁር እና የቀድሞው የባሕር ኃይል ባልደረባ ናቸው። ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ መነሻ እና መዳረሻ እንደኾነ ተናግረዋል።
ቀይ ባሕር የሀገሪቱ ወሰን በመኾኑ ያለፉት ዘመናት ነገሥታቶችም ያሥተዳድሩት እና ይገለገሉበት እንደነበር ገልጸዋል። አጼ ካሌብ በቀይ ባሕር እጅግ የዳበር የባሕር ኃይል እንደነበራቸው ነው ያጣቀሱት።
ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመንን እና ደቡብ አረቢያን ተቆጣጥረው ሲያሥተዳድሩት እንደነበር ነው የጠቆሙት። አጼ ዘርያዕቆብም ቢኾን ከ1434 እሰከ 1468 ዓ.ም በነበረው የንግሥ እና ዘመናቸው ቀይ ባሕርን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ሲያሥተዳድሩት እንደነበር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባላት ጥንታዊ የወደብ ታሪክ እስከ የመን፣ ፑትላንድ ሶማሌ፣ አረብ ምድር እና የኩሽ ምድር ጠረፍ ድረስ የንግድ ልውውጥ ስታደርግ የነበረው የቀይ ባሕር ዳርቻ ባለቤት ሥለነበረች ነው ብለዋል።
የቀይ ባሕር ቀጠና ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ የገባቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን አፍሪካን ለመቀራመት በመጡ ጊዜ ግብጽ ከካይሮ እስከ ሱዳን፣ ከሶማሌ እስከ ኢትዮጵያ ሞምባሳ ድረስ ያለውን ክልል ለመቆጣጠር አቅዳ መዝመቷንም አንስተዋል።
ይህ ሁሉ ሲኾን ግን ግብጽ በራሷ አቅም ብቻ አልነበረም ለመውረር የተነሳችው። ከአውሮፖ የቀጠረቻቸውን ወታደራዊ ኃይሎችን በማዝመት ነው ብለዋል።
ጅኦፖለቲካ ማለት የአንድ አካባቢ የጅኦግራፊ፣ የስራቴጅ፣ የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚ ሁኔታዎች መስተጋብር መገለጫ እንደኾነ የገለጹት ሌፍተናንት ኮማንደር በርባ አቶሚሳ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ብሔራዊ ህልውና ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ጅኦፖለቲካ ጋር በጥብቅ እና በጥልቅ የተቆራኘ ነው ብለዋል።
ቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጠረፎች እና ወሰኖች ኢትዮጵያን ከሁሉም አህጉራት ጋር የሚያገናኙ በሮች እና ድልድዮች መኾናቸውን ነው በአጽንኦት የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቀይ ባሕር እና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ፣ ለሀገሪቱ ዕድገት እና ጥፋትም መሠረት ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።
ቀይ ባሕር በሲውዝ ቦይ አማካኝነት ከሜድንትራንያን ባሕር ጋር የተገናኘ እንደመኾኑ መጠን የዓለም የገቢ እና የወጪ ንግዶች እስከ ሩቅ ምሥራቅ እና ጃፓን ድረስ ይተላለፍበት እንደነበርም ያስታወሱት ሌፍተናንቱ “ሁለት ሦስተኛው የዓለም ንግድ የሚተላለፈው በቀይ ባሕር እንደኾነም” ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ወቅትም በቀይ ባሕር የነገሱ የንግድ እና የጦር መርከቦቿም በቀይ ባሕር መልህቃቸውን ዘርግተው ዘመናትን ተሻግረዋል።
ከቀይ ባህር እስከ ሕንድ ውቂያኖስ ድንበር ከአንደኛው የወደብ መነሻ ወደ ሌላኘው የወደብ መዳረሻ አስሰዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ በክብር እና በኩራት ተንሸራሽረዋል። ይህም ኢትዮጵያን በታሪክ ገጽ እንድትገለጽ እና በዓለም አደባባይ ጎልታ እንድትታወቅ አድርገዋታል።
በድካም የማይዝሉ፤ በእንቅልፍ የማይፈዙ የባሕር ኃይሎቿ የቀይ የባሕር ክልሏን ለማስጠበቅ አያሌ መስዕዋት ከፍለዋል። ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቂያኖስ ድንበር አስሰውታል። በልበ ሙሉነት፣ በክብር እና በኩራት ተመላልሰውበታል።
ቀጣናውን በባለቤትነት እና በበላይነት አሥተዳድረውታል። ቀይ ባሕር ዛሬ ላይ የአልሸባብ እና አይ ኤስ አይ ኤስ፣ የሑቲ አማጽያን እና የሽብር ቡድን የዘረፋ፣ እገታ እና ግድያ ወንጀል የሚፈጽምበት ይሁን እንጅ የትላንት ኢትዮጵያውያን የባሕር ኃይሎች የቀይ ባሕር ቀጣናን ሠላም እና ደኅንነት በማስከበር አይተኬ ሚናን ተጫውተዋል።
ቀን እና ማታ ውርጭ እና ቁሩ ያልበገራቸው እነዚህ ትንታግ ልጆቿ የሉዓላዊነት መከበሪያቸው፣ ብሔራዊ ኩራታቸው እና የህልውና መሠረታቸው፤ የባሕር ወደብ ኾነና ውሎ አዳራቸው ቀይ ባሕር እንደነበር የቀድሞው የባህር ኃይል ባልደርባ ሌፍተናንት ኮማንደር በርባ አቶሚሳ ተናግረዋል።
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እና ብሔራዊ ደኅንነት ወሳኝ ይሁን እንጅ በዘመኑ በነበሩ ብሔርተኞች፣ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ጠላት ኃይሎች በተበተቡት ሴራ እና በጠነሰሱት ተንኮል የባሕር በሯን እና የባሕር ክልሏን እንድታጣ አድርገዋታልም ነው ያሉት።
የምሥራቅ አፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልውና ከዓባይ ሸለቆ እና ከቀይ ባሕር ጅኦፖለቲካ ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህም ነው ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ብሎም ለዓለም የደም ሥር ነው የሚባለው።
“ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የታሪክ መነሻ ብቻ ሳይኾን የደም ሥር መብቀያም ነው” ብለዋል። ህልውናችን የበቀለው እና ታሪካችን የተቀዳው ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆዎች ነው። “የታሪክ መዳረሻችን እና የህልውና መሠረታችንም ቢኾን ቀይ ባሕር እና ዓባይ ነው”።
የኢትዮጵያ ህልውና እና የሥልጣኔ ታሪክ ከሁለቱ ጉዳዮች ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል።
የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጠረፎች እና ወሰኖች የሀገሪቱ የንግድ መግቢያ እና መውጫ በሮች በመኾን ያገልግሉ እንጅ የውጭ ጠላት ኃይሎች መግቢያ እና መውጫ በር በመኾን ብሔራዊ የደህንነት ሥጋት ኾነውም ለዘመናት ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ሦስት አራተኛው ጦርነት የተከሰተባት በቀይ ባሕር እንደነበርም አንስተዋል። ፋሽስቱ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው በቀይ ባሕር በኩል አድርጎ ነው። ግብጽ እና ሌሎችም ቢኾኑ የተንኮል ሴራቸውን፤ የበቀል መርዛቸውን ኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም አቅደው የመጡት በዚኸው በቀይ ባሕር አድርገው ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ወሳኝ የወጭ እና የገቢ ንግድ ማሳለጫ ከኾኑት ወደቦች አንዱ የአሰብ ወደብ ነው። ይህን ወሳኝ ስትራቴጂያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ጥንታዊ ወደቧ የንግድ ብቻ ሳይኾን ወታደራዊ መተላለፊያዋ ኾኖ እስከ 1990ዎቹ መባቻ ድረስ በባለቤትነት ተገልግላበታለች።
ዘመናትን በባለቤትነት ስታሥተዳድረው እና ስትገለገልበት የነበረው የአሰብ ወደብ አንጡራ ሃብቷን ካጣች ጀምሮም ብሔራዊ የህልውና አደጋ ተጋርጦባት ሦስት አስርት ዓመታትን ተሻግራለች።
ኢትዮጵያ እሰከ 1983 ዓ.ም የግዛቷ አንድ አካል በኾነው የአሰብ ወደብ የወጭ እና የገቢ ንግዷን ስታከናውን መቆየቷ ትውልድ የማይረሳው ታሪክ የሚዘክረው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ኢትዮጵያ ትላንት የአሰብ ወደብ ባለቤት ለመኾኗ በጥቁር ቀለም የተከተቡ የታሪክ ድርሳናት እና መዛግብትን ማገላበጥ ሳያሻ እነዚህ አንደበቶች ህያው ምስክር ናቸው።
በዘመኑ የነበሩ የባሕር ኃይል አባላት እና የወደቡ እንደራሴዎች አስረግጠው ይመስክራሉ። የቀይ ባሕር እና አሰብ ጉዳይ ሲነሳባቸው ትላንትን ተመልሰው በትዝታ ሲያስታውሱት እልህ እና ቁጭቱ ብሶባቸው እንባ ይተናነቃቸዋል።
ብሔራዊ ኩራቷ የኾነው የጦር ሰፈሯን አመድ ሲለብስ፤ የባሕር ኃይሏ እንደጉም ሲተን፣ ተፈርቶ እና ተከብሮ የቆየው የባሕር ክልሏም በወንበዴዎች ሲደፈር፣ የንግድ እና የጦር መርከቦቿ የኔ ባይ አጥተው ሲዘረፉ እና በቆሙበት ሰምጠው ሲቀሩ፣ አሉኝ የምትላቸው የወደብ አንጡራ ሃብት እና ንብረቶቿ የባሕር ሲሳይ ኾነው ሲቀሩ ማየትም፣ መስማት ምንኛ ከባድ ነው።
ይህ የታሪክ እጥፋት ለትላንት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የቁጭት እንጉርጉሮ ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ይሁን እንጅ በደሉ በዚህም አላበቃም አዲሱ ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር ምንነት እና አስፈላጊነት እንዳያውቅ፣ የባሕር በር ባለቤት ለመኾን እንዳይቆጨው እና እንዳይሞግት፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ዝና እና ክብር በእልህ እና በቁጭት ለማስመለስ የድርሻውን እንዳይወጣ ጉዳዩ ተዳፍኖ ቆይቷል።
እንዳውም ለሀገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት እና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ቁልፍ እና ወሳኝ ቦታ እንደኾነ የሚነገርለት የአሰብ ወደብ ከግመሎች ውኃ ማጠጫነት የዘለለ ፋይዳ የለውም ሲሉም ተዘባብተውበታል።
በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሣኤ በደም አፋሳሹ የኢትዮ ኤርትራ የነበረውን ጦርነት እና መንግሥታቸው ስለ ባሕር በር የነበረውን አቋም ከኤን ቢሲ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንጸባርቀዋል።
በወቅቱ የባሕር በር ጉዳይ በብሔራዊ አጀንዳነት እንዲነሳ አይፈቀድም ነበር ብለዋል። በሀገር ወዳድ ምሁራን ሲነሳም ከድጋፉ ይልቅ ተቃውሞው ይበረታል ነው ያሉት። በወቅቱ የፖለቲካ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ እንጅ ሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤት የመኾን ዕድል እንደነበራት ነው በአጽንኦት የተናገሩት።
ታዲያ ይህ ታሪካዊ ክስተት በትላንቱ ትውልድ ወቀሳ እና ትችትን አስተናግዶ ይለፍ እንጅ ለዛሬው ትውልድ ግን ትላንት እየታወሰ በጸጸት እና በትዝብት የሚያልፍ አይመስልም።
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ለማግኘት ብሔራዊ አጀንዳ አድርጋ ወደ ሥራ ገብታለች። አዲሱ ትውልድ ትናንት ማስተዋል ከጎደላቸው መሪዎች የተረከበውን ዕዳ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ የባሕር በር ባለቤት ሊኾን እና ትናንት ሀገሩ በባሕር በር የነበራትን ክብር እና ዝና ሊመልስ ሽርጉድ ማለቱን ቀጥሏል።
በእርግጥ ይህ ትውልድ 130 ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለመኖሯ ብሔራዊ የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባት የተረዳው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀን ብሔራዊ አጀንዳ አድርገው በዓደባባይ ከተናገሩ ማግስት ነው።
ትውልዱ ብሔራዊ ጥቅሙን እና ደኅንነቱን ሊያስከብር፣ ሉዓላዊ ክብሩን ሊያስጠብቅ፣ የታሪክ ተወቃሽ ላለመኾን እና በአጠቃላይ ዘመን የጣለበትን ሀገራዊ እና ታሪካዊ ኀላፊነት ሊወጣ የባሕር በርን በአጀንዳነት ይዞ ወደ ፊት ብሏል።
ምሁራን የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ መኾኑን የሚዘክሩ የታሪክ መዛግብትን እያጣቀሱ እውነታውን ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እወቁልን እያሉ ነው። የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ እንጅ የኤርትራ ኾኖ አያውቅም በማለት ሀቁን ደፍረው የሚመሰክሩላት የትላንት የባሕር ኃይል አባላትም ነፍሳችንም ስጋችንም ቀይ ባሕር ነው ብለዋል።
የዓለማቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ሳይንስ ሊሂቃኖቿም የዘመናት የቁጭት እንጉርጉሮ ይብቃ ብለው ለዚህኛው ትውልድ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን የሚያስታጥቅ፣ የጀግንነት እና የአይበገሬነት ወኔን የሚያላብሱ ታሪካዊ እና ሕጋዊ እውነታዎችን እንኩ ተቀበሉ ብለዋል።
የታሪክ ጸሐፍትም ቢኾን ታሪክን ሳያንኳሱ እና ሳያጋኑ፤ ሳይጨምሩ እና ሳይቀንሱ ከእነ ነፍሱ እና ከእነ እውነቱ በደመቀ ብራናቸው፤ በረቀቀ ብዕራቸው የኢትዮጵያን ዘመን አይሽሬ የባሕር በር ታሪክ ከትበው ለተደራሲያን አድርሰዋል።
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጉምቱ ፖለቲከኞች እና ዓለማቀፍ ዲፕሎማቶቿም ቢኾን ሀገራቸው የባሕር በርን ከጎረቤት ሀገራት አንድም በስትራቴጅካዊ ወዳጅነት አልያም ሰጦ በመቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ እንድታገኝ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃንም ቢኾን ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች እና በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን ተጠቅማ ማግኘት እንደምትችል ለዓለማቀፉ ማኅበረስብ በማሳወቅ ሚናቸውን እየተወጡ ነው።
ብቻ በጥቅሉ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበረውን ሕዝባዊ ተሳትፎ እና የተገኘውን ድል በባሕር በር ለመድገም ሁሉም በየፊናው ርብርቡን ቀጥሏል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሳየውን ተሳትፎ እና አንድነት የተቀዳጀውን ድል እና ክብር በአንድነት በመቆም በባሕር በርም ሊደግመው እንደሚገባ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ምሁሩ እና የቀድሞው የባህር ኃይል ባልደረባው ሌፍተናንት ኮማንደር መርባ አቶምሳ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleግብረ ገብነታችን ከልብ ይሁን።
Next article“በክብር የነገሡት፤ በግርማ የታጀቡት”