
ባሕር ዳር:- ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ለእንግዳ በሚደረግ መስተንግዶ ቤተኞቹም ስንሳተፍ ቸር እንግዳ አምጣ እንላለን። ለእንግዳው ቅቤ፣ ማር፣ ወተት እና ሌላም ይቀርባል። ሌሎች በዕለት ከዕለት የማይደረጉ እንክብካቤዎችም ለእንግዳው ይደረጉለታል።
ታዲያ ለእንግዳ መቀበያ ተብሎ ከተደበቀበት ከሚወጣው መስተንግዶ ለአባዎራው እና ቤተ ዘመዱም ስለሚሳተፍ ”ቸር እንግዳ” አምጣ ተብሎ ይተረባል።
ሁል ጊዜ ለራስ የማይጠቀሙትን ለእንግዳ ክብር ሲባል የሚደረግ ይህ ዓይነቱ መስተንግዶ ሌላውን አክባሪነት ስለኾነ አይነቀፍም።
ነገር ግን ሁል ጊዜ ማድረግ እየቻልን ሰው፣ ጊዜ እና ሁኔታ ጠብቀን ብቻ የምናደርጋቸው ባህሪያት እና ተግባራትም አሉን።
በፖሊስ ጣቢያ እና በፍርድ ቤት አካባቢ ስንሄድ በጥንቃቄ እና በፍርሃት ሕግ አክባሪ እንኾናለን። በሃይማኖት ተቋማት እና በሕዝብ መሐል ስንኾንም ትሁት እና “ቀኝ ጉንጫችንን ሰጪ” ያደርገናል።
ወጣቶች በሰፈራቸው ሰዎች ፊት እና በሌላ ቦታ የሚኖራቸው አስተውሎት፣ ልጃገረዶች በመምህሮቻቸው ፊት ሲኾኑ እና በሌላ ቦታ የሚኖራቸው ጭምትንት እና ጥሞና ተቃራኒ ሲኾን ይስተዋላል።
አሽከርካሪዎች ትራፊክ ፖሊስ ሲያዩ ሕግ አክባሪ ለመምሰል የሚያደርጉት ጥንቃቄ፣ ፍርሃት እና መሽቆጥቆጥ፤ የቀበሌውን ሊቀመንበር ጉዳይ የማይሉት አርሶ አደሮች ”የበላይ አካል” ሲመጣ ያላቸው ትህትና ይለያል።
ብቻ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አምኖበት በራሱ አነሳሽነት ሁልጊዜ ቢፈጽመው በምጣኔ ሃብት፣ በጤና፣ በሕግና ሥርዓት፣ በደኅንነት እና በግብረ ገብነት ተጠቃሚ የሚያደርጉን በርካታ የየዕለት ክዋኔዎች እና መስተጋብሮች አሉን። ከሕግ እና የሞራል ተጠያቂነትም ነጻ የሚያደርጉ ናቸው።
ችግሩ ግን የምንፈጽማቸው ለታይታ ከኾነ ነው። የትራፊክ ሕግ ብናከብር ደኅንነታችን የሚጠበቀው እኛው ኾነን ሳለ ትራፊክ ስናይ ብቻ ነው ሕጉን የምናከብረው። የእግረኛ መንገድ፣ የቀበቶ ማሰር፣ ቅድሚያ ለእግረኛ መስጠት፣ ረጋ ብሎ ማሽከርከር ትዝ የሚለን፤ ትራፊኩን በመፍራት ነው።
ከሃይማኖት ተቋማት ግቢም ፍጹም ግብረገብ ስንመስል በሌሎች ቦታዎች ግን ‘ኑ ግጠሙኝ’ ለማለት የደረስን ትዕቢታም እንኾናለን።
ለሰው ታይታ ብለን በአንዳንድ ቦታዎች የምንፈጽማቸውን መልካም ነገሮች ሁልጊዜ ብንተገብራቸው ምን ችግር አለው? እንደ ማርና ቅቤው አያልቁብን!
ቤተክርስቲያን፣ መስጊድ ወይም ሌሎች የእምነት ቦታዎች አካባቢ የሚንቀሳቀስ ሰው እርጋታው ትኅትናው ወዘተ ለሃይማኖቱ መንፈሳዊ ኃይል ክብር ሲል ነው ብለን ብናስብ ያከበራቸው እነዚያ መንፈሳዊ ኃይላት በሌላ ቦታም የሉም የሚል አስተምህሮ የለም፤ ነገርግን እርጋታ እና ትህትናውን በሌላ ቦታ አንደግመውም። ለምን?
ለትዳር አጋሮቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ንጹሕ እና ማራኪ ለመኾን እምብዛም የማይጣጣሩ ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ ግን ለመዋብ መስታዎት ፊት በርካታ ደቂቃዎችን ያሳልፋሉ።
ቅቤ፣ ማር፣ ወተት እና የመሳሰሉ ውድ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎቹን የድሎት አኗኗሮች በየዕለቱ ለመጠቀም የምጣኔ ሃብት አቅማችን ስለሚገድበን ለእንግዳ ብቻ ብናደርግለት እንግዳ አክባሪነት ልንለው እንችላለን።
ሁልጊዜ ብንተገብራቸው የማያልቁብንን ጠቃሚ እሴቶች የማንተገብራቸው ግን ሕግ ወይም ጉልበተኛ ካላየን በስተቀር የሞራል ግዴታን ስለማናከብር ነው ብዬ አስባለሁ።
አሁን አሁንማ ቀድሞ ነበሩን የምንላቸው እና የምንኮራባቸው የሞራል እሴቶቻችንም እየተሸረሸሩ እና እየተተው ነው። የነበረን አንተ ትብስ አንቺ ትብሺ መከባበር አሁን ላይ በእኔ ልቅደም እኔ ልቅደም ጭቅጭቅ እና ጠብ እየተተካም ይመስላል።
ሥርቆት እና ነጥቆ መሮጥም ድሮም ነበር ብንልም የዘመኑን ምክንያቱ እና አድራጎቱን ላጤነው ግን ያስፈራል። የደካሞችን በደል እንደራሱ በማየት ለተበዳዮች ቆሞ ግንባሩን ይሰጥ የነበረ ማኅበረሰብ ዛሬ ዛሬ ከፊቱ ላይ ገድለው ቢኼዱ ነገ ምስክርነት ላለመጠራት ባላየ ፊቱን የሚያዞረው የትየለሌ ሳይኾን ይቀራል?
ሁሉንም ነገር በመንግሥት እና በመንግሥት አካላት በማመካኘት ከንፈር የመምጠጠን አባዜ ትተን የሞራል እሴቶቻችንን ካላጠናከርን በስተቀር ችግሩ ከዚህም ሊከፋብን ይችላል ባይ ነኝ።
ሥርዓተ መንግሥት ሰዎች የሚገዙበት የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የምጣኔ ሃብት፣ የባሕል እና የደኅንነት ፍልስፍና ድንጋጌ እና መስተጋብር ነው። በዚህ ሁሉ ደግሞ ሁላችን አለን። እያንዳንዳችን በዕለት ከዕለት ሕይወታችን ለሕግ፣ ለሞራል እና ለበጎ ባሕሎቻችን ተገዝተን ብንኖር የምናነሳቸው ህጸጾች ላይበራከቱ ምናልባትም ላይኖሩ ይችላሉ።
እንደ ሌሎች ችግሮቻችን በቴክኖሎጂ መዘመን፣ በሉላዊነት፣ በኑሮ ውድነት እና በሰላም እጦት ጨርሰን የምናመካኝባቸውም አይደሉምና።
እናም በተናጠልም ኾነ በጋራ ሕይዎታችን ማስመሰሉን ሳይኾን እውነተኛውን፣ ሕግን ፈርተን ሳይኾን ወድደን፣ ለአጭር ጊዜ ሳይኾን ለዘላቂው ብንሠራ እና ብንኖር መልካም ነው እላለሁ።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
