መልካም እሴቶቻችን መመለስ የምንችለው በበጎ ተግባራት ላይ ስንሠማራ ነው።

18
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቸገሩ ወገኖችን እና አረጋውያንን መርዳት ከመልካም እሴቶቻችን ውስጥ ይጠቀሳሉ። የተስፈኞቹ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላት በሰቆጣ ከተማ ለሚገኙ የተቸገሩ ወገኖችን በሳምንት ሁለት ቀን ይደግፋሉ።
ወጣት አክሊሉ እንዳለው ማኅበሩን ከተቀላቀለ አራት ዓመቱ ሲኾን ጸጉር በማስተካከል፣ ደም በመለገስ እና የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመጠገን የበኩሉን አሥተዋጽኦ ማድረጉን ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
“መልካም እሴቶቻችንን መመለስ የምንችለው በበጎ ተግባራት ላይ ስንሠማራ ነው” ይላል ወጣት አክሊሉ።
ሌላኛዋ የተቸገሩ ወገኖችን ጸጉር ስትሠራ ያገኘናት ወጣት እመቤት አወቀ መልካም ነገር ማድረግ ውስጣዊ እርካታን የሚሰጥ ትልቅ ጸጋ ነው ብላለች። በቀጣይም በበጎ ተግባር መሳተፏን እንደምትቀጥል ነው የገለጸችው።
ወይዘሮ የሽወርቅ አባተ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ ማየት የተሳናቸው እናት ናቸው። ባለፉት 12 ዓመታት ከቤተ ክርስትያን በር ደጅ ጠንተው በሚያገኙት ሳንቲም ይኖሩ እንደነበር አጫውተውናል። የተስፈኞቹ በጎ አድራጊ ወጣቶች የሚያደርጉላቸው ድጋፍ ተስፋቸውን እንዳለመለመው ተናግረዋል። በየጊዜው ስለሚያደርጉላቸው ድጋፍ እና ክትትልም ምስጋና አቅርበዋል።
የተስፈኞቹ በጎ አድራጎት ማኅበር ከተመሠረተ 10 ዓመቱ ሲኾን ከ150 በላይ በጎ አድራጊ ወጣቶችን ያቀፈ ማኅበር ነው።
ወጣቶቹ በየሙያ ዘርፋቸው የተቸገሩ ወገኖችን እየረዱ እንደሚገኙ የተናገሩት የበጎ አድራጎት ማኅበሩ መሥራች እና ሰብሳቢ ወጣት ቢኒያም ዋለልኝ ነው። በቀጣይም የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባሻገር ማኅበሩን ለተቸገሩ ወገኖች ማረፊያ ድርጅት ለማድረግ አቅደው እየሠሩ መኾኑንም ተናግሯል።
በሰቆጣ ከተማ ከሚንቀሳቀሱ የወጣቶች ማኅበራት ውስጥ ተስፈኞቹ ያለማቋረጥ የተቸገሩ ወገኖችን የሚደግፉ የመልካም ወጣት ምሳሌ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሚካኤሌ ሢሣይ ናቸው።
እየጠፋ ያለውን መልካም እሴት ለመመለስ ተስፈኞቹ የጀመሩት ተግባር ቀላል አይደለም ያሉት ኀላፊው የወጣቶቹን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያጠናክሩ ባለሃብቶች እና አጋዥ ድርጅቶች በግብአት እና በበጀት እንዲደግፏቸውም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን መርቀን ስንከፍት ደስ ይለናል” አጼ ኃይለ ሥላሴ
Next articleግብረ ገብነታችን ከልብ ይሁን።