
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ሥርጭት በኢትዮጵያ የተጀመረው በአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ነበር።
በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሥብሠባንም ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዚህ ሳምንት ዘገባ ይዞ ብቅ ያለው።
በሥብሠባው ላይ በታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች የተደረጉት የተለያዩ ንግግሮች ተቀርጸው ለኢትዮጵያውያን በቴሌቪዥኑ መስኮት ተላለፉ።
ጉባኤውም በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ለሚገኘው ነዋሪዎች እንዲሠራጭ እና በወቅቱ በመላው አፍሪካ ላይ እየተካሄደ ስለነበረው የነጻነት ትግል እና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን በቴሌቪዥን መስኮቱ አማካኝነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደረገ።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ በመደበኛ ሁኔታ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲያደርግ ኾኖ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት ተቋቋመ።
በምርቃቱ ወቅትም አጼ ኃይለሥላሴ “ለሕዝባችን ትምህርት እና ዕውቀት ለማካፈል የሚቻልበትን ዘዴ በመሻት ለምናደርገው ጥረት ቴሌቪዥን ተጨማሪ መሣሪያ ስለሚኾን “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን መርቀን ስንከፍት ደስ ይለናል” በማለት ተናገሩ።
መደበኛ ሥርጭቱን በዚህ ሳምንት ጥቅምት 23/1957 ዓ.ም አንድ ብሎ ለተመልካቾቹ አስተላለፈ። መደበኛ ሥርጭቱም ከምሽቱ 11:30 እስከ 5 ሰዓት የዘለቁ የተለያዩ የዜና እና የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ መርሐ ግብሮችን ያካተተ ነበር።
ምንጭ ፦አዲስ ዘመን ጋዜጣ
ደራሲ እና ጋዜጠኛ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል በደብረ ብርሃን ከተማ ገርም ገብርኤል አጥቢያ ልክ በዚህ ሳምንት ጥቅምት 23 ቀን 1909 ዓ.ም ነበር የተወለዱት።
ከኢትዮጵያ አንጋፋ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አንዱ የኾኑት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ከበደ ሚካኤል ከሚጽፉት የግጥም ሥራ በተጨማሪ ሥራዎቻቸውን ደጋግመው በመጻፍ እና ስህተቶችን ነቅሰው በማውጣት ለትውልድ የሚበጁ መጽሐፍትን አበርክተዋል፡፡
ደራሲ ለመኾን የሚያበቁትን ስልቶች ለተደራሲው ከመጠቆማቸውም ባሻገር የተማረ ሰው ዕውቀቱን ለኅብረተሰቡ የማካፈል ኀላፊነት እንዳለበትም ያሳስቡ ነበር፡፡
“የቅኔ ውበት” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው እንዳስነበቡት ብዙ ድርሰቶቻቸው ከሌሎች ጸሐፍት የተወረሱ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሁሉም ሥራዎቻቸው በውርስ ድርሰቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ ካለመኾናቸውም በላይ አብዛኛዎቹ ድርሰቶች የራሳቸው የአዕምሮ ውጤት መኾናቸውን ዘርዝረዋል፡፡
የደራሲ እና ጋዜጠኛ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ሥራዎች ልቦለድ ታሪኮች፣ የተውኔት ድርሰቶች ላቅ ያሉ ሥነ ጽሑፋዊ ለዛ ያላቸው ግጥሞች፣ ትውፊታዊ እና ታሪካዊ የሥነ ጽሑፍ ቃና ያላቸው ግጥሞች ይገኙባቸዋል፡፡
ደራሲ እና ጋዜጠኛ ከበደ ሚካኤል የቋንቋ ችሎታ ስለነበራቸው በአንዳንድ ደራስያን ሥራዎች ውስጥ የሚታዩት ለአማርኛ እንግዳ የኾኑ ቃላት እና ሐረጋት በድርሰቶቻቸው ውስጥ ፈጽሞ አይታዩም፡፡
አቀራረባቸውም ግልጽ በመኾኑ ሊያስተላልፉት የፈለጉትን መልዕክት ለአንባብያን ፍንትው አድርጎ የማሳየት ችሎታም ነበራቸው ፡፡
“አኒባል” እና “ካሌብ” በተሰኙት ሁለት የመድረክ ድርሰቶቻቸው ከኢትዮጵያ ባሕል እና ወግ ወጣ በማለት የአፍሪካን ጥንታዊ ገናናነት ሊያሳዩ የሚችሉ ሥራዎችን ለአንባብያን አቅርበዋል ፡፡
በእነዚህ ሁለት የመድረክ ሥራዎቻቸው ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከዘመኑ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ቀድመው ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሀሳብ ያመላከቱ ደራሲም ናቸው፡፡
ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ በየደረጃው የተዘጋጀ የማስተማሪያ መጽሐፍ ችግር በመኖሩ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ከበደ ሚካኤል”ታሪክና ምሳሌ 1ኛ መጽሐፍ 3ኛ ክፍል” የሚል ርእስ በመስጠት በ1934 ዓ.ም ያሳተሙት መጽሐፍ በዚያን ጊዜ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩ ወጣቶች ማስተማሪያነት እንዲውል ተደርጎም ነበር፡፡
ከበደ ሚካኤል በ1950 ዓ.ም ያሳተሙት “ብርሃነ ኅሊና” የተሰኘው ሥራቸው የምንኖርባትን ዓለም በትዝብት መነጽር ለመመልከት ተጠቅመውበታል፡፡
ደራሲ እና ጋዜጠኛ ከበደ ሚካኤል ወደ 30 የሚጠጉ መጻሕፍትን ሲጽፉ ጥቂት የመድረክ ተውኔቶችንም አዘጋጅተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸው በሰዎች ሥነ ምግባር ላይ የሚያተኩሩ እና ምክር አዘል መልዕክቶችን የማስተላለፍ ዝንባሌ ይንጸባረቅባቸዋል።
ዘመናዊት ኢትዮጵያን በዕውቀት ለመገንባት በተደረገው ርብርብ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት እኒህ ባለቅኔ፣ ጸሐፊ-ተውኔት፣ ደራሲ፣ አንጋፋ ጋዜጠኛ እና የቀለም ሰው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትን ይሁንታ በማግኘት በቀዳሚነት ሽልማት ተቀብለዋል ፡፡
ለሀገራቸው ላበረከቱት የረጅም ጊዜ አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 26/1990 ዓ.ም በሥነ ጽሑፍ የክብር ዶክትሬት ዲግሪም ሸልሟቸዋል።
ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና ከሜክሲኮም ሽልማት ተቀብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ዳይሬክተር፣ የብሔራዊ መጽሐፍት ቤት ዳይሬክተር እና የካቢኔ ሚኒስትር ኾነው እንዳገለገሉም የቅኔ ውበት መጽሐፋቸው ያስረዳል።
ምንጭ፦ ብላክ ላየን መጽሐፍ እና የባለታሪኩ ድርሰት
እ.ኤ.አ. በ 1859 የስዊዘርላንድ ነጋዴ ሄንሪ ዱናንት በሰሜናዊ ጣልያን አካባቢ እየተጓዘ ሳለ በፍራንኮ-ሰርዲኒያ እና በኦስትሪያ ጦር መካከል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሶልፈሪኖ ትንሽ መንደር አቅራቢያ ኾኖ ተመልክቷል።
ጦርነቱ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ላይ ጉዳት ያደረሰ ነበር፡፡ ይህን ጉዳት በቅርበት የተመለከተው ሄንሪ ዱና አላስችልህ ሲለው እነዚህን የተጎዱ ሰዎች የሚታደግበትን መንገድ ያወጣ ያወርድ ጀመር፡፡
እ.ኤ.አ. በ1862 ዱናንት በጦርነቱ ለተጎዱ ወታደሮች ሊረዱ የሚችሉ የሠለጠኑ በጎ ፈቃደኞችን ያቀፉ ብሔራዊ የእርዳታ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ የሚያስችል “ኤ ሚሞሪ ኦፍ ሳልፋሪኖ” የተሰኘ መጽሐፍም አሳተመ።
በመጨረሻም የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በመባል የሚታወቀውን ድርጅት በመመሥረት በጦር ሜዳ ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎችን ለመለየት በነጭ ጀርባ ላይ የቀይ መስቀል ምልክትን እንዲጠቀሙ አደረገ።
ቀይ መስቀል በስዊዘርላንድ በ1863 የተመሠረተ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅት ሲኾን በዓለም ዙሪያ በአደጋ፣ በትጥቅ ግጭት እና በጤና ቀውሶች ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ነው።
ዱናንት ከየትኛውም ወገን ምንም ይሁን ምን በጦርነት ለተጎዱ ወታደሮች እርዳታ ሊሰጥ የሚችል የሠለጠኑ በጎ ፈቃደኞችን ያቀፈ ብሔራዊ የእርዳታ ድርጅት እንዲቋቋም ተሟግቷል። ድርጅቱም እንዲመሠረት ማድረግ ችሏል፡፡
ለተጎዱ ሰዎች አባት የኾነው ይህ ሰው በዚህ ሳምንት ጥቅምት 20/1910 ዓ.ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡
ምንጭ፦ ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
