
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 11 ይከበራል፡፡ ቀኑ በዚህ ዓመትም በኢትዮጵያ ለስምንተኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ “የእኔን ለውጥ የምመራ ታዳጊ ሴት ልጅ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ወይም የልጃገረዶች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክን በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች መሪዎች፣ መምህራን እና ታዳጊ ሴቶች በተገኙበት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ የፖናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ ተማሪ ናርዶስ ተክላይ የታዳጊ ሴቶች ወይም ልጃገረዶች ቀን መከበሩ ሴቶችን ያበረታታል ብላለች። ስለ ሴቶች ጥቃት ምንነት እና ጥቃት ሲፈጸም ምን ማድረግ እንደሚገባ ግንዛቤ ለማስጨበጥም ያግዛል ነው ያለችው።
ሴት ልጆችን ከወንዶች ጋር አኩል አድርጎ አለማየት፣ በራሷ እንድትወስን ያለመፍቀድ እና ሴቶችን ወደኋላ የሚያስቀሩ አስተሳሰቦች እንደሚስታዋሉ ተናግራለች።
ነገር ግን ሴት ልጅ አቅም ያላት እና ጥበበኛ መኾኗን ተገንዝቦ ማኅበረሰቡ ዕድል መስጠት ይኖርበታል ነው ያለችው፡፡ ሴት ልጆችም ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው ብላለች። ጥቃት ሲደርስ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳለባቸውም ተናግራለች፡፡
ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ተማሪ ኤልሳቤጥ አስናቀ የበዓሉ መከበር ታዳጊ ሴቶች ስለመብቶቻቸው እና ጥቃትን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስችላል ብላለች፡፡ ታዳጊ ሴቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ ወላጆች፣ መምህራን፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት ተቋማት ብዙ ይጠበቅባቸዋል ነው ያለችው፡፡
በመድረኩ የተሳተፉት መምህር አስካለ ማርያም አለኸኝ በትምህርት ቤታቸው ታዳጊ ሴቶችን በክበብ በማደራጀት የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
የልጃገረዶች ቀን መከበሩ ልጆቹ ግንዛቤያቸው ከፍ እንዲል ያግዛልም ብለዋል፡፡ “ታዳጊ ሴቶች ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ የቀለም ትምህርት ብቻውን በቂ አይደለም” ብለዋል። በተጓዳኝ ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ አብዛኞቹ ችግሮች የሚመጡት በግንዛቤ ችግር ምክንያት በመኾኑ ለመከላከል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ግንዛቤ፣ ንቅናቄ እና ተሳትፎ ዳይሬክተር ደስታ ፈንታ በታዳጊ ሴቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
አሁንም ቢኾን ችግሮች አሉ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ልጃገረዶች የአቻ ግፊትን በመቋቋም ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር ልጃገረዶችን ለማብቃት በትኩረት የሚሠራበት ነው ብለዋል። ልጆችም እርስ በእርስ በመማማር ራሳቸውን እንዲያበቁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው “በታዳጊ ሴቶች ላይ እየተስተዋለ ያለው ጥቃት ጾታዊ ብቻ አይደለም” ብለዋል፡፡ ጥቃቱ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊም ነው፤ የዲጂታል ሚዲያውን በመጠቀም የሚደርሱ ጥቃቶች በርካታ በመኾቸው ወላጆች ልጆቻቸውን መከታተል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
እንደተቋም ችግሩን ለመፍታት ዋናው መፍትሔ ግንዛቤ ማስጨበጥ በመኾኑ በስፋት እየተሠራበት ነው ብለዋል፡፡ ከትምህርት ገበታ ውጪ የኾኑ ሴት ልጆች ለጥቃት ተጋላጭ በመኾናቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ትምህርት እንዲሔዱ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ ጥቃት ሲያዩ በተዘጋጀው 7722 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
