
አዲስ አበባ: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሩሲያውያን እንደ እ.ኤ.አ 1612 ከፖላንድ ቀኝ ግዛት ነጻ የወጡበትን የነጻነት ቀን እያከበሩ ይገኛሉ
ቀኑም ሩሲያውያን በመደብ በብሔር እና ሌሎች ሁነቶች የማይለያዩበት፣ እኩል ዜጋ የኾኑበት ዕለት ተደርጎ የሚከበር የአንድ በዓል ነው።
ቀኑን አስመልከቶ በአዲስ አበባ የሩሲያ የባሕል እና ትምህርት ማዕከል ፑሽኪን አዳራሽ የስዕል እና ኪነ ጥብብ ኤግዚቪሽን እና ዐውደርእይ ተከፍቷል።
ኤግዚቪሽን እና ዐውደርእዩን የከፈቱት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር እቭጊኒ ተርኪኺን መከፋፈል እና አንድ አለመኾን የኋላቀርነት መገለጫ ነው ብለዋል።
አንድነት የችግሮች ሁሉ መፍትሔ፣ የዘመናዊ ሀገር ግንባታ መሠረት እንደኾነም አስረድተዋል።
ሀገራቸው ሩሲያ ብዙ አስቸጋሪ እና ውሥብሥብ ጉዳዮችን እንዳለፈችም ነው ያብራሩት። ቀኑን ሲያከብሩም በአያቶቻቸው እንደሚኮሩ እና በዘመናዊ ሀገር ግንባታ ያለፉ ዜጎችን እንደሚያመሠግኑ ተናግረዋል።
በዝግጅቱ የታደሙት ሩሲያዊቷ አክሳና ብሩዚክ ይህ ቀን የሀገራቸውን ባሕል ለማሳደግ የበኩላቸውን የሚያደርጉበት እና ለልጆቻቸው አንድነትን እና ባሕልን የሚነግሩበት እንደኾነም ተናግረዋል።
በዓሉ ከሌሎች ሀገራት ዜጎች ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያሳድጉበት ልዩ ቀን እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ቀኑ ከታላላቆቻቸው ስለ ሀገሯ ፍቅር እንዲማሩ ያደረጋቸው መኾኑን ለአሚኮ ገልጸዋል።
እሳቸውም ለልጆቻቸው የሀገራቸውን ታሪክ እንደሚነግሩ እና ስለሀገር ፍቅር እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል።
የሩሲያ የአንድነት ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ስዕሎችን ያዘጋጁት አርቲስት ተስፋሁን ክብሩ በዓሉ የሩስያውያንን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን እና ባሕልን በስዕል ለሌሎች ለማሳየት ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
የስዕል እና ኪነጥበብ ኤግዚቢሽኑ ለቀጣዮቹ ሳምንታት ይቆያል። የሁለቱን ሀገራት የባሕል ትስስር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያሳድጋልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
