የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት በደብረ ብርሃን ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።

15

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጥነው ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለተመደቡ የመደበኛ እና አድማ መከላከል የፖሊስ አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛቸው ለገሰ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት ትልቅ ሕዝባዊ ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ካጋጠመው የሰላም መደፍረስ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ ከሕዝቡ ጋር በመኾን ይሠራልም ነው ያሉት።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ገብረመስቀል ቦጋለ አሁን ያለውን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ በመታገል ሰላም እንዲፈጠር እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የሕዝብ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ አዳዲስ እና ነባር የፖሊስ አባላት በጋራ በመኾን በልዩ ትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለውጤት እንዲበቁ ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል።

ሕዝቡ ሰላም ወዳድ ነው ያሉት ኮማንደር ንጉሴ የፖሊስ አባላት በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

በመርሐ ግብሩ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በግዳጅ አፈጻጸም የተሻለ ጀብድ ለፈጸሙ የመደበኛ እና አድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የማዕረግ እና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

አቀባበል የተደረገላቸው የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት መንግሥት እና ሕዝብ የጣለብንን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሰላምን ለማጽናት በሚሰሩ ሥራዎች ሕዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል ወታደራዊ መሪዎችን ጨምሮ ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የጸጥታ አካላት እና መሪዎች ተሳትፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የጸጥታ አካላቱ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሠሩ ነው።
Next articleየተፋሰስ ልማት ሥራው ምርታማነት በመጨመር ተጨባጭ ለውጦችን አምጥቷል።