
ጎንደር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር “የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዥት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት በከተማው ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅር አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና ሌሎችንም የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ለመከወን የሚያስችሉ ሃሳቦች ተነስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም ከገጠመው የጸጥታ ችግር ለመውጣት መድረኩ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለሰላም መረጋገጥ ወሳኝ ሚና ካላቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ካለፉት ጊዜያት በተሻለ በከተማዋ አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ያረጋገጡት ኀላፊው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የጸጥታ አካላቱ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ስጋት ነፃ እንዲኾን ለማስቻል ብሎም ለኅብረተሰቡ ምቹ እና ሰላም የሰፈነበት አካባቢን ለመገንባት ከዚህ ቀደም ያላቸውን አበርክቶ አጠናክረው የሚቀጥሉ መኾኑን ነግረውናል።
ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ ትቀጥላለች ያሉት ኀላፊው ለዚህ ደግሞ የጸጥታ አካሉ ያለበት አደራ ከፍ ያለ መኾኑን አንስተዋል።
ሃሳባቸውን ያጋሩት የውይይቱ ተሳታፊ የጸጥታ አካላት በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ሢሠሩ መቆየታቸውን ነግረውናል።
በቀጣይም ከሀገር እና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ቁርጠኛ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዥት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን ለማስመዝገብ ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
