
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ “የእኔን ለውጥ የምመራ ታዳጊ ሴት ልጅ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ወይም የልጃገረዶች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 11 ቀን ሲከበር መቆየቱንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያም ለስምንተኛ ጊዜ “የእኔን ለውጥ የምመራ ታዳጊ ሴት ልጅ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት እስከ ቀበሌ ድረስ በየደረጃው በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር ዓላማው ታዳጊ ሴቶች ራሳቸውን እንዲያበቁ፣ መሪነት እንዲለማመዱ እና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲፈቱ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በክልሉ ታዳጊ ሴቶችን ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመከላከል የጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ኮሚቴ ጥምረት ተደራጅቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ችግሮች ሲከሰቱም ከፍትሕ አካላት ጋር በመኾን ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በዓሉ የሚከበረው ታዳጊ ሴቶች በክበባት ተደራጅተው ለመብቶቻቸው እንዲታገሉ ለማስቻል መኾኑንም ገልጸዋል።
ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑትን የመመለስ እና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ወላጆቻቸው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሠማሩ እና ልጆች እንዲማሩ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩም ገልጸዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች መሪዎች፣ መምህራን እና ታዳጊ ሴቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
