
ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከጠላት መንጋዎች ተጠብቃለች፤ ከነጻነቷ ሳትጎድል ዘመናትን ተሻግራለች፤ ሉዓላዊነቷን አስከብራለች፤ በልጆቿ አንድነት እና የጸና ጀግንነት በድል ኖራለች፤ በአሸናፊነት ከብራለች።
ጠላቶች ያላትን ሊነጥቋት፤ ሀብቷን ሊያሳጧት፤ ነጻነቷን ሊቀሟት፤ ክብሯን እና ማንነቷን ሊወስዱባት ያለ ማቋረጥ ፈተና አብዝተውባታል፤ ግንባር እየፈጠሩ ዘምተውባታል፤ አዝምተውበታል፤ ጦር እያሾሉ ወርውረውባታል። እርሷ ግን የተወረወረባትን እየቀለበች፤ የዘመቱባትን እየመከተች፤ ሳይነኳት የነኳትን እየቀጣች፤ እግር ያነሱባትን አደብ እያስገዛች ጠላቶቿን ሁሉ በድል መልሳለች ኢትዮጵያ።
በዘመናት ሥልጣኔዋ፣ በዘመናት የጀግንነት እና የአይደፈሬነት ታሪኳ ውጭ የሌላን ሀገር ሀቅ አልነካችም፤ የማይገባትን አልጠየቀችም፤ የሌላን ወሰንም አልደፈረችም። ነገር ግን ሀቋንም አሳልፋ አልሰጠችም፤ ወደፊትም አትሰጥም። ለሀቋ እና ለክብሯም ሸብረክ አላለችም።
ስለ ምን ቢሉ እርሷ የሌላን አትነካም፤ የራሷንም አትሰጥምና። ኢትዮጵያ የዓለም የጂኦፖለቲካ፣ የጂኦግራፊ እና የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል ናት። የቀይ ባሕር እና የዓባይ እመቤት ኢትዮጵያ ሁለቱ የውኃ አካላት የወዳጆቿም የጠላቶቿም መምጫዎች ናቸው። ጠላቶቿ ሃብቷን ሊወስዱ ወዳጆቿ ደግሞ ሃብቷን መሠረት አድርገው ወዳጅነታቸውን ሊያጠናክሩ።
ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የሥልጣኔ፣ የጥንታዊ የአፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ አሕጉራት እና ሕዝቦች የመገናኛ ጎዳና እና ድልድይ በኾነው በቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ ክልል የምትገኝ የአፍሪካ ኃያል መንግሥት እና ሥልጣኔ መገኛ ናት ብለው ጽፈዋል።
ከጥንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕልውና ሕይዎት እና ታሪክ ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ የጂኦፖለቲካ ጋር በቅርብ እና በጥብቅ የተያያዘ ነው ይላሉ።
ጂኦፖለቲካ የአንድ አካባቢ ወይም ሀገር የጆኦግራፊ፣ የስትራቴጂ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መስተጋብር እና መግለጫ ነው። በዚህ አኳያ በስትራቴጂያዊው የአፍሪካ ቀንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ብሔራዊ ሕልውና፤ ሕይዎት እና ነጻነት ከሁለቱ ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ ጋር በቅርብ እና በጥብቅ የተያያዘ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለቀይ ባሕር እና ለዓባይ ሸለቆ ጠረፎች እና ወሰኖች ወሳኝ ሚና የሰጡ ጅኦግራፊያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስትራቴጂካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ሁኔታዎች ብዙ ናቸው ነው የሚሉት።
የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጠረፎች እና ወሰኖች ኢትዮጵያን ከውጭው ዓለም ጋር የሚያገናኙ በሮች እና ድልድዮች ናቸው። ሁለቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጠረፎች እና ወሰኖች ከጥንት ጀምረው የሀገሪቱ ዋና የንግድ መግቢያ እና መውጫ በሮች ናቸው ብለዋል።
በሁለቱም ታሪካዊ ጠረፎች እና ወሰኖች አማካኝነት ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምራ ከአካባቢው የአፍሪካ እና የእስያ ሕዝቦች ጋር የቆየ እና የጠበቀ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ግንኙነቶች መሥርታለች።
ሁለቱም የበዓዳን ወረራ በሮች ናቸው። ከዚህም የተነሳ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ ጠረፎች እና ወሰኖች ዓለም አቀፋዊ ሰላም እና ጸጥታ መፈለግ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ዓላማ እና ተግባር መኾኑን ታሪክ ይመሰክራል ይላሉ።
ታዲያ በእነዚህ ወሳኝ ሥፍራዎች ላይ የጠላቶች ዓይን ከመነጣጠር ተቋርጦ አያውቁም። ሁልጊዜም ጠላቶች የሚመጡት በእነዚህ በኩል እንደኾነም ነው የገለጹት።
ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ታሪካዊ ጠረፎች በኢትዮጵያ ምድር እና ሕዝብ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በሥፍራ እና በጊዜ ያልተቋረጠ አዲስ የወራሪዎች እና የኢምፔሪያሊስቶች ጥቃት እና ጥፋት ሲሰነዘር ኖሯል ነው የሚሉት።
እነዚህ ጠላቶች ኢትዮጵያ በወንዟ በዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ጫና አስከመፍጠር፤ የቀይ ባሕርን ባለቤትነቷን እንድታጣ እና የባሕር ክልሏ ሌላ ሀገር እንድትኾን እስከማድረግ ደርሰዋል ነው ያሉት።
ያም ኾኖ ግን ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታቸውን በጀግንነታቸው እና በአንድነታቸው አስከብረዋል። የቀይ ባሕር ባለቤትነታቸውንም ለማስመለስ በቁርጠኝነት ተነስተዋል።
ፕሮፌሰሩ ሲጽፉ ጂኦፖለቲካ በአንድ ሀገር ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አካባቢው እና እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረታዊ የዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ወይም አፍራሽ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የጅኦግራፊያዊ፣ የስትራቴጂ፤ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መግለጫ እና መስተጋቢር ነው ይላሉ።
በዚህ ረገድ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ረጅም የነጻነት ታሪክ እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና ሂደት በሀገሪቱ ብሔራዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ መሠረታዊ የልማት አስተዋጽኦ እና የአፍራሽ ተጽዕኖ ፈረቃ ሲያስከትል ኖሯል ነው የሚሉት።
በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ ላይ የተነሳው ዓለም አቀፍ የኢምፔሪያሊዝም እና የፋሽዝም ግፊት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የግብጽ መንግሥታት ክተት በኢትዮጵያ በቀይ ባሕር፣ በዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ ላይ አፍራሽ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የውጭ ተጻራሪ ኃይሎች በልዩ ልዩ መንገዶች እና ወቅቶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ማኅበራዊ የዕድገት ጎዳና ላይ ብዙ እንቅፋቶችን በመፍጠር ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚገኝበት ኋላቀር የዕድገት ደረጃ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ታሪክ ያስተምረናል ነው የሚሉት።
ለወደፊቱም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በፍጥነት አዲስ ብሔራዊ የጠረፍ ዕድገት እና ልማት ፖሊሲ እና ፕሮግራም ቀይሶ ተግባራዊ እስኪያደርግ ድረስ ምናልባትም በሀገሪቱ አጠቃላይ ብሔራዊ ዕድገት እና ልማት ጉዳይ ላይ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ አፍራሽ ተጽዕኖ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችል ይኾናል ብለዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው በጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ የውጭ ኃይሎች የዳህላክን ደሴት እና ሌሎች የኢትዮጵያ ይዞታዎች ተቆጣጥረው የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ወደብ እና የወደቡን ከተማ ካፈራረሱ በኋላ ሉዓላዊነታችን ለመዳፈር ሲሞክሩ ኖረዋል ብለው ጽፈዋል።
የኢትዮጵያን የቀደመ ግዛት እና የባሕር ክልል ለመቆጣጠር የሚመጡ የውጭ ጠላቶችን የኢትዮጵያ ጀግኖች ጽናት፣ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት የጠላቶችን መስፋፋት ሲመክት ኖሯል ብለዋል በጽሑፋቸው።
የሥልጣኔዎቿ አብነቶች የኾኑትን የዓባይን ተፋሰስ እና የቀይ ባሕርን ክልል ለመያዝ ከውጭም ከውስጥም ያልተነሳ ጠላት አልነበረም። የዓለም ውድ እና ተፈላጊ የኾኑ ሃብቶች ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ ጠላቶች ከጥንት ጀምሮ የባሕር በር የሌላትን ኢትዮጵያን ለማየት ፍላጎታቸውም ኾነ ምኞታቸው እንደነበር ጽፈዋል።
መንግሥቱ ሲጽፉ አፍሪካን ለመቀራመት የወሰኑ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ኢትዮጵያን ለመውረር በመንደርደሪያነት የሚያገለግሏቸውን ስትራቴጂካዊ ሥፍራዎችን መርጠው ነበር። በኢትዮጵያ ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ እና ምሥራቅ ክልሎች የሚገኙትን ስምንት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ያላቸውን የባሕር በሮች ተከፋፍለው በመክበብ ኢትዮጵያን የማፈን ሥራ ሠርተዋል ይላሉ።
ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባሕርን፣ የሕንድ ውቅያኖስ እና የዓባይ ሸለቆን ተቆጣጥረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ለመቀራመትም ያላደረጉት ጥረት አልነበረም ነው የሚሉት።
በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠላቶች የኢትዮጵያን ባሕር፣ የባሕር ክልል እና ወደቧን ለመውሰድ ሲረባረቡ ኖረዋል ብለው ጽፈዋል። የኢትዮጵያ ነገሥታትም የባሕር በራቸውን ላለማጣት ሲዋደቁ ኖረዋል ነው ያሉት።
የታሪክ እና የባሕል ተመራማሪው ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር በጀግንነት ጸንታለች፤ ነጻነቷን፣ ወሰኗን፤ ክብሯን አስጣብቃ ኖራለች ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ በዘመናት ጉዞዋ ውስጥ ፈተናዎች ቢደራረቡባትም ብሔራዊ ጥቅሞቿን ስታስከብር ኖራለች የሚሉት ፕሮፌሰሩ ብሔራዊ ጥቅም በሰላማዊ መንገድ እና በጦርነት ይከበራል፤ ኢትዮጵያም ሰላምን እያስቀደመች ብሔራዊ ጥቅሞቿን ስታስከብር ኖራለች ይላሉ። በብሔራዊ ጥቅሞቿ ላይ በጉልበት የመጡትን ደግሞ በጀግንነት ስትመክት የኖረች ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ናት፤ አቀማመጧ ፈተና የበዛበት ነው፤ የውጭ ጠላቶችም ፈተናዎችን ደቅነው ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል እየነሳች ክብሯን አስጠብቃ ዘልቃለች ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር በብቸኝነት ነጻ የኖረች፤ ነጻነቷን ያላስነካች፤ ቀንዲል ኾና የዘለቀች ናት ይሏታል።
ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ ለዘመናት ይዛው የኖረችውን የባሕር በር በታሪካዊ ስህተት አጥታ ቆይታለች፤ ነገር ግን የባሕር በሯን ጊዜ ይወስድባት ካልኾነ በስተቀር መመለሱ አይቀርም ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ድርሻዋን ማግኘቷ አይቀርም፤ የኢትዮጵያ የቀድሞ ወደቦች የግመል መፈንጫ ኾነው የሚቀሩ አይመስለኝም፤ አንድ ቀን መመለሳቸው አይቀርም ይላሉ።
ቀይ ባሕርን ሁሉም ይመኛዋል፤ አስፈላጊ እና ወሳኝ ስለኾነ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ያገለለ አካሄድ አይሠራም፤ ኢትዮጵያ በነጻነት ብቻ ሳይኾን በሰላም ማስከበር ሥራ በዓለም ታላቅ ስም አላት፤ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ላይ የሰላም ሁኔታው ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራት የባሕር ድርሻ ያስፈልጋታል ነው የሚሉት።
የቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስን ሰላም ለማስከበር ኢትዮጵያ ታስፈልጋለች፤ በውይይት ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት ማድረግ ይገባል፤ ኢትዮጵያን በውይይት የባሕር በር ማድረግ ይቻላልም ይላሉ።
የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ሕግ እና ታሪክ ይደግፋታል፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን የመጠቀም መብት አላት፤ የባሕር በርን መጠቀም ከድህነት መውጫ ነው፤ ኢትዮጵያን ከባሕር በር መከልከል ምቀኝነት ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያን ጥያቄ ለማስመለስ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰሩ የውስጡን ግጭት የሚያባብስ የውጭ ተጽዕኖ አለ፤ የውጩን አባባሽ ጉዳይ ማየት አለብን፤ ኢትዮጵያ የዓባይ እና የቀይ ባሕርን ከተጠቀመች በአፍሪካ ቀዳሚ ትኾናለች የሚል ስጋት አለ፤ ይህን ስጋት ለማስቀረት ደግሞ የውጭ ጠላቶች የውስጥ ግጭት እንዲነሳ እና እንዲባባስ ያደርጋሉ ነው የሚሉት።
የውጭ ጠላቶች መጀመሪያ አፍሪካን የሚፈልጓት ጉልበቷን ነበር፤ ቀጥለው መሬቷን እና ሀብቷን ነው የፈለጉት፤ ተፈጥሮ የሰጠውን ጸጋ እንዳንጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፤ ይህን በደንብ መረዳት ይገባል፤ ለእነሱ ሃሳብ መሰሪያ አንሁን፤ ተባብረን ችግር እንፍታ እንጂ ተባብረን ችግር አናምጣ ነው ያሉት።
ከመገዳደል፣ ከግጭት በመውጣት ወደ ሰላም መምጣት ይገባል፤ አዋጩ እና ማሰሪያው ውይይት እና ሰላም ነው፤ ግጭት ማንንም አይጠቅምም ነው የሚሉት። የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ ያድራል ያሉት ፕሮፌሰሩ በፉክክር ሀገር አይጠቀምም፤ በስምምነት ነው ሀገር የሚጸናው ብለዋል።
ባሕር ሥልጣኔዋ የተሠራበት፣ ታላቅነቷ የተገነባበት፣ ከዓለም ሀገር የተሳሰረችበት፣ ማንነቷ በዓለም ላይ ጎላ ብሎ የታየበት ሀብቷ ነውና ታገኘዋለች።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
