
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር” የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዥት በማምከን አንጸባራቂ ድሎች እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ከወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ከከተማዋ የተውጣጡ ወጣቶች ታድመዋል። ወጣቶች ዘላቂ ሰላም እና ሀገራዊ እድገት ላይ ስለሚኖራቸው አበርክቶ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በተቋማት የሚሰጥን አገልግሎት ከእጅ መንሻ የተላቀቀ በማድረግ ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል ወጣቶቹ፡፡
ከተማ ግብርናን ጨምሮ ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ጸጋን ለይቶ ስምሪት መስጠት ላይ አሁን ካለው ጅምር በላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
በወጣቶች በኩልም ያለውን የሥራ ባሕል ማሳደግ እንደሚገባ ተገልጿል። ራስን ለመለወጥ መንቀሳቀስ የሚጠበቅ እንደኾነም በዕለቱ ተገልጿል።
የወጣቶችን ጤና፣ ሥነ ልቦና እና አምራችነት የሚጎዱ እንደ ሱስ እና የመሳሰሉ መጤ ጎጂ ልማዶች በከተማዋ እንደሚስተዋሉም ተነስቷል።
ከተማዋን የሚመጥኑ፣ ትውልድ የሚያንጹ እና የመዝናኛ አማራጭን የሚያሰፉ የወጣት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባት እና ማልማት እንደሚጠበቅም ተወያዬች ጠይቀዋል፡፡
በሰላም እጦቱ ይበልጥ ከተፈተኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶች መኾናችን የገለጹት ተሳታፊዎቹ ለችግሩ መፍትሔ በመኾን በኩልም ከእኛ ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ግጭት የብዙ የፍላጎት እጆች አሉበት፣ ሰላማችንን በራሳችን ለማስጠበቅ እና ለምንናፍቀው እድገት መሠረት ነውና “ለሰላም መስፈን ከቤተሰቦቻችን በመጀመር ድርሻችንን እንወጣለን” ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወጣቶች ክንፍ ኀላፊ ኃይለማርያም ወንድምሸት እንደ ሀገር ሰላምን፣ አብሮነትን እና የጋራ ማንነትን የሚያሳድጉ በርካታ እሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የችግሮችን መነሻ በጥልቀት በመመልከት ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል ኀላፊው፡፡
የወጣቶች የመማር ጉዳይ፣ ተንቀሳቅሶ የመሥራት እና የመለወጥ ጉዳዮች እንዲስተካከሉ ሰላም ትልቁ እና ለድርድር የማይቀርብ መኾኑንም ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አውራሪስ አረጋ ወጣቶች ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ መፍታት፣ የጋራ መፍትሔ ማፈላለግ እና የወል ትርክት ግንበታን በማጽናት ድርሻቸው ግዙፍ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ከተሳሳተ ትርክት በመውጣት በወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስ ወጣቶች ለሰላም እና ለዘላቂ ልማት በጎ አሻራችን ትቶ ማለፍ የትውልድ ኀላፊነታቸው መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የውስጥ ሰላምን በማጠናከር ከውጭ ለሚመጡብን ከፋፋይ ጉዳዮች በአንድነት መመከት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ አውራሪስ፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አይናለም ከፈለኝ ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የሚመጡ የሥራ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ያሉ ዝንፈቶች ፈጥነው መስተካከል እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
የዲጂታላይዜሽን አሠራር በመተግበሩ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የአሠራር መጓተቶች እና ችግሮች በአንጻራዊነት መቀረፋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
