
ጎንደር: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ”የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት በጎንደር ከተማ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ ሰላምን በማስፈን የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። በከተማው እየተሠራ ያለውን የኮሪደር ልማት የሚደገፉ መኾኑን በዕለቱ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
ወጣቶቹ ጅምር የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
በከተማው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የወጣቶች ማኅበር እንዲጠናከር፣ በቂ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እና ወጣቶችን ያማከለ የመዝናኛ ቦታዎች እንዲገነቡም በትኩረት አንስተዋል።
ወጣቶቹ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ አለመኾኑን እንረዳለን ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወጣቶች ክንፍ ኀላፊ ቶፊቅ እስማኤልሀኪም ናቸው።
ለወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤታቸው በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራም አንስተዋል። ወጣቶችን ማደራጀት፣ ለወጣቶች የክህሎት ሥልጠና መስጠት እና የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የአጼ ፋሲል ስታዲየም ግንባታ 25 በመቶ መጠናቀቁን ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሩ መሐመድ ሌሎች በከተማው የተጀመሩ ሁለት ትናንሽ ሜዳዎች በቀጣይ ሦስት ወራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።
ወጣቶች የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን እና የኅብረተሰቡን እሴቶች እንዲጠብቁም አሳስበዋል። ማኅበራዊ ሚዲያን ለመልካም ተግባር እንዲገለገሉም አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ እና የከንቲባ ተወካይ ነጻነት መንግሥቴ በከተማው ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅም ይሠራል ነው ያሉት።
በቀጣይም ለወጣቶች ተጠቃሚነት እና የጋራ አደረጃጀት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ሐሰተኛ ትርክትን በእውነተኛ መረጃ ማጋለጥ፣ ሕዝባዊ የሰላም አደረጃጀቶችን መፍጠር እና ማጠናከር በቀጣይ ሊሠራባቸው የታቀዱ ተግባራት መኾናቸውም በውይይቱ ተነስቷል።
ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
