
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ፅጌ ዓለማየሁ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ወረዳ ዋድ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማቆያ ክፍል አገልግሎት እያገኙ ነው አሚኮ ያገኛቸው።
የእናቶች ማቆያ ክፍሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ለመውለድ የተቃረቡ ነፍሰ ጡር እናቶችን ማረፊያ ሰጥቶ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ይገኝበታል።
ወይዘሮ ጽጌ ዓለማየሁ መኖሪያ ቤታቸው ከጤና ተቋሙ የራቀ በመኾኑ እና ተሽከርካሪ እንደልብ የማይገባበት በመኾኑ ወደ እናቶች ማቆያ ለመግባት እንደተገደዱ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፅጌ ዓለማየሁ በማቆያው በሕክምና ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ባለው እንክብካቤ መደሰታቸውን ገልጸው በጤና ጣቢያው የተገነባው የእናቶች ማቆያ በወሊድ ወቅት ሲያጋጥም የነበረውን የእናቶች ሞት እና እንግልት ያስቀረ መኾኑንም መታዘባቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ፅጌ ማቆያው በርካታ ወላድ እናቶችም እንዳሉበት ገልጸው እንደቤታቸው ኾኖ እያገለገላቸው እንዳለ እና የጤና ባለሙያወቹም ክትትል የሚመሠገን ነው ብለዋል።
የዋድ ጤና ጣቢያ ኀላፊ አብርሃም ፍሬው እናቶች እና ሕጻናትን መንከባከብ ግዴታቸው እንደኾነም ጠቁመዋል። ኀላፊው እንደተናገሩት እናቶች ተገቢውን ክትትል እና እንክብካቤ ሲያገኙ ጤናማ ትውልድን መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
አሁን ላይ የተጀመረው የወላድ እናቶች ማቆያ እናቶችንም ኾነ ቤተሰቡን ከጭንቀት እና ከእንግልት የገላገለ እንደኾነም አስረድተዋል።
ራቅ ያለ ቦታ ላይ የምትመጣን እናት የአምቡላንስ አለመኖር እንዲሁም ወቅቱ በፈጠረው የሰላም እጦት ችግር እንደልብ መንቀሳቀስ ስላልተቻለ መውለጃዋ ሲዳረስ ጀምሮ በማቆያው በማስገባት ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ከቤታቸው ባልተናነሰ መልኩ ወልደው እስኪሄዱ ድረስ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የእናቶች ማቆያን ለማጠናከር ከየቀበሌው መሬት በመቀበል እና በማልማት ለእናቶች የምግብ ወጭዎች እና እነሱን ለሚረዱ የኮንትራት ሠራተኞች አገልግሎት እያዋሉት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
የደምበጫ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በልስቲ ዳኛቸው የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ጤናን ለመጠበቅ የእናቶች ማቆያ ፋይዳው ከፍ ያለ መኾኑን ገልጸዋል።
በወረዳው ስድስት ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን እና በሁሉም ተቋማት የእናቶች ማቆያ እደተዘጋጀ ተናግረዋል።
እንደ ጽሕፈት ቤትም የእናቶች እና ሕጻናትን ጤንነት ለማስጠበቅ ተከታታይነት ያለው የቤተሰብ ዕቅድ እና የነፍስጡር እናቶች ክትትል በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በወረዳው በሠለጠነ እና የጤና ባለሙያዎች ከወለዱ 1ሺህ 218 እናቶች መካከል 666ቱ እናቶች ስምንት ጊዜ ክትትል ማድረጋቸውን ኀላፊው ተናግረዋል።
በወረዳው ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ሁለት የእናቶች አንቡላንስን በመውሰዳቸው እናቶች በቤት እንዳይወልዱ በጤና ጣቢያ በተሠሩ የእናቶች ማቆያ እንዲቆዩ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ካለው ወቅታዊ ችግር አኳያ የእናቶቹን ሞት ለመቀነስ እንደ ደምበጫ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት በገጠር አካባቢ ያሉ ወጣቶችን በማደራጀት ቀደም ባለው ጊዜ ይጠቀሙበት እንደነበረው በቃሬዛ ወላዶቹ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡበትን መንገድ እንዳመቻቹም ገልጸዋል።
በቀጣይም በእናቶች ማቆያ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን በሁሉም ጤና ጣቢያዎች ለመሥራት ማቀዳቸውንም አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች እና የአፍላ ወጣቶች አሥተባባሪ አዲስ ዘመን ጫኔ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከወጣቶች እርግዝና ጀምሮ የማያቋርጥ ተከታታይነት ያለው አገልግሎት በጤና ተቋማት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የእናቶች ማቆያ በጤና ተቋማት እንዲጠናከሩ እየተሠራ ይገኛል ያሉት አሥተባባሪዋ የመውለጃ ጊዜያቸው የደረሱ እናቶች ወደ ማቆያ መጥተው እንዲወልዱ በመደረጉም የእናቶች ሞትን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በክልሉ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እንደ ሀገር በጤና ፖሊሲ የተቀመጡ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛልም ነው ያሉት።
አሥተባባሪዋ እንደ ክልል የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ጤናን ለመጠበቅ የእናቶች ማቆያ ውጤት ማስገኘቱንም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እና የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ግብ ተጥሎ አየተሠራ ይገኛል ያሉት አሥተባባሪዋ ያለ ዕድሜ እርግዝና እንዳይፈጠር የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።
በክልሉ ለእናቶች እንደሚደረገው የጤና እንክብካቤ ሥራ ለሕጻናትም ተገቢው አገልግሎት እየተሰጠ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
