
ደሴ: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወቅታዊ የሰላም ጉዳይን በተመለከተ ከወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦት ሰውን፣ ምጣኔ ሃብትን፣ ነጻነትን፣ ፍቅርን እና መተማመንን የሚያጠፋ የሁሉም ነገር ጸር እንደኾነ አንስተዋል።
ጦርነት አስከፊነቱ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣
ስደት እና ሌሎች ችግሮችን ማስከተሉ ብቻም ሳይኾን ከዚያ በኋላ መልሶ የነበረን ሥነ ልቦና ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርጋል ነው ያሉት።
በክልሉ ባለው የሠላም እጦት የተነሳ ወጣቶች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት ባለመቻላቸው ለሥራ አጥነት፣ ለሱስ፣ ለሥነ ልቦናዊ ጫና እና ለሌሎች ችግሮች ተጋልጠዋል ነው ያሉት።
የመልካም ሥነ ልቦና ጉድለት ደግሞ ሰዎች በሀገራቸው ተስፋ እንዲቆርጡ በማድረግ ስደትን፣ የሥራ ተነሳሽነት ማጣትን እና አጥፊነትን ያስከትላል ብለዋል።
“እርስ በእርስ መጠፋፋት ማንንም አሸናፊ አያደርግም” ያሉት ተሳታፊዎቹ ሁሉም አካል ለሰላም እና ተቀራርቦ ለመነጋገር የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ሀገራዊ እሳቤን በማዳበር የባሕር በርን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች እውን ይኾኑ ዘንድ የመንግሥት አቅም ለመኾን እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል አማካሪ አወል አሕመድ ሀገር የምትለማው ሕዝቦች ተከባብረው በሰላም ሲኖሩ ነው ብለዋል። ሰላምን ለማስጠበቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከተማዋ ሰላሟን አስጠብቃ እንድትቀጥል ወጣቶች የሰላም ዘብነታቸውን አሳይተዋል ያሉት ኀላፊው ከልማቱ ተጠቃሚ ለመኾን በቀጣይም አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ የድርሻውቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በመድረኩ “የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዥት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ጸጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
