
ጎንደር: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበረሰባዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የወገራ ወረዳ እና በሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ወረዳ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የሁለቱ ወረዳ አሥተዳደሮች “ዘላቂ ሰላም ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ማኅበረሰባዊ የምክክር መድረክ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መሪዎች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተገኝተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮነን ማኅበረሰቡን በማወያየት እና የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘመኑን እና የአማራን ሕዝብ ክብር በማይመጥን ኋላቀር እሳቤ የሚደረግ የጦርነት እንቅስቃሴ ሊቆም እና ችግሮች በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር በርካታ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ አካላት በምኅረት ማስገባት መቻሉንም አብራርተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል ወርቁ የሁለቱን ወረዳ ወንድማማች ሕዝብ በጋራ ማወያዬት መቻሉ አንድነትን እና ትብብርን ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብም በንቃት ሰላሙን እንዲጠብቅ እና ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የዳባት ወረዳ አሥተዳዳሪ መርሻ ወረታ ማኅበረሰቡ እየደረሰበት ካለው ሁለንተናዊ ችግር እንዲወጣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ጎን ተሰልፎ ለሰላም መስፈን እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚበረታታ እና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።
ከሁለቱ ወረዳዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው የጸጥታ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለሰላም በአንድነት ሙሉ ኀይልን ተጠቅሞ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ መዋቅር አባላት በቁርጠኝነት ባደረጉት ርብርብ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
