
ደብረታቦር፡ ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት እና ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉብኝት ተካሂዷል።
ወይዘሮ አስቴር በዛ በንግድ ሥራ የተሰማሩ የደብረታቦር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ጨርቃጨርቅ እና የባሕል አልባሳትን የሚያመርተው ድርጅታቸው ለ20 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
አሁን ላይ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ውስንነቶች እንዳሉበት የገለጹት ወይዘሮ አስቴር የጸጥታ ችግሩን ምክንያት በማድረግ ሥራ ያቋረጡ እና የግንባታ ሂደትንም የሚያጓትቱ ባለሃብቶች ሀገርን ለማልማት ቁርጠኛ ሁነው ወደ ሥራ እንዲገቡ መክረዋል።
ሌላኛው ሃሳባቸውን ለአሚኮ ያጋሩት አቶ እጹብ ጌጡ ለዘመናት የነበረው የመብራት ችግር መፈታቱን አንስተዋል። የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲነቃቃ ባለሃብቶችና የመንግሥት አካላት በመመካከር የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም የነበረው የጸጥታ ችግር ብዙ ጉዳቶችን ቢያስከትልም አሁን ላይ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ማኅበረሰቡን ማገልገልና ወደሥራ መመለስ ይገባል ነው ያሉት።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አስራት መሰለ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በጋራ በመነጋገር ወደ ሥራ መግባት ይገባል ነው ያሉት። የሦስተኛ ወገን እና የመሠረተ ልማት ጉድለቶችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ወደ ሥራ ላለመግባት በቂ ያልኾነ ምክንያት በማቅረብ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንዳይኾን የሚያደርጉ ባለሀብቶች መኖራቸውንም አንስተዋል። በእነዚህ ባለሃብቶች ላይም ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ ተገቢ የእርምት ርምጃ እየተወሰደ ነውም ብለዋል።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊና የከንቲባ ተወካይ ይበልጣል ጌታቸው መብራት፣ ቦታና የጥሬ እቃ አቅርቦት በባለሀብቶች በኩል በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮች መኾናቸውን አንስተዋል። ችግሮቹም እየተፈቱ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም መብራትን የተመለከተው የዘመናት ችግር መፈታቱን አንስተዋል።
በከተማዋ ለማልማት ለሚመጡ ባለሃብቶች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሰላም እጦቱ ባለሃብቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዳይገቡ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አንስተዋል።
በከተማዋ የአየር ማረፊያ ቢሠራ ለልማት ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። 
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		