የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል የመስኖ ልማት ቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል።

8

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስኖ ልማት እና የተቀናጀ ተፋሰስ ልማትን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ከመምሪያው እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የሥራ ኀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተቀናጀ የመስኖ ልማትን ለማሳደግ የሚያስችል የጋራ ውይይት የተካሄደ ነው።

ሁሉንም የመስኖ አማራጮች መጠቀም እንደሚገባ እና በዝናብ ብቻ ጥገኛ ከመኾን ለመላቀቅ በቅንጅት ለመሥራት የንቅናቄ ሥራ ማስጀመራቸውን የተናገሩት የግብርና መምሪያ ኀላፊው መርሻ አይሳነው ናቸው።

በዘንድሮው የመስኖ ሥራ 2 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማም ኀላፊው ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥ ስንዴ 1ሺህ 500 ሄክታር መሬት ይለማል ያሉት ኀላፊው ከ63 ሺህ ኩንታል በላይ ምርትም ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

6 ሺህ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ሥራ የሚሳተፉ ሲኾን በአጠቃላይ 190 ሺህ ኩንታል ይጠበቃል ነው ያሉት።

የምርት እድገትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥረት እንደተደረገም ነው የተናገሩት። 8 ሺህ ኩንታል የሠው ሠራሽ ማዳበሪያ እና 400 ኩንታል ምርጥ ዘር ለመጠቀም መታቀዱንም አንስተዋል።

የመስኖ ልማት ሥራችንን ውጤታማ ለማድረግ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን የገለጹት አርሶ አደሮቹ የመስኖ ልማት ሥራ ኢኮኖሚዊ ለውጥ እያስገኘላቸው መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አበበች የኋላሸት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እየተሠራ ነው።
Next articleለአልሚ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መኾኑን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።