
ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገር ልማት እና ዕድገት ትልቅ ፀጋ የኾነውን የመሬት ሃብት በአግባቡ መምራት እና ማሥተዳደር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ተግባር ነው።
ይህን ሃብት በቁጠባ ለመጠቀም እና ለማሥተዳደር ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ እንደኾነም ይነገራል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ለ10ሺህ ባለ ይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ ኀላፊ መኮንን ደባሱ ተናግረዋል።
በከተማው የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ በመከላከል ግልጽ የኾነ አሠራር ለመዘርጋት እና በመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
መሬትን በዘመናዊ መንገድ ለማሥተዳደር በተደረገው ርብርብ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ ከ10 ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስመለስ መቻሉን ነው ያስረዱት።
የመሬት ማስተላለፍ እና ዝውውር ሥርዓት ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ እንዲፈፀም በማድረግ የከተማ መሬትን እንደ የአገልግሎቱ ለይቶ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል በጋራ እየተሠራ መኾኑም ተብራርቷል።
ማኅበረሰቡ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ አሠራሮች ሕጋዊ መስመር እንዲይዙ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		
