
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሒሳባቸው ኦዲት ተደርጎ የከፋ የኦዲት አስተያየት ከተሰጣቸው እና ካላስተካከሉ ተቋማት ጋር የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ ነው።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የአዲስ ዓለም ሆስፒታል፣ የአማራ ክልል የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል፣ የሀን ጤና ጣቢያ እና የዱርቤቴ ሆስፒታል የኦዲት ግኝትን ሪፖርት አቅርቧል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ በተደረገ ውይይትም የየተቋማቱ ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች አንዳንዶቹ ግኝቶች በተቋማቸው የሥራ ባህሪ የተፈጠረባቸው መኾኑን ጠቅሰዋል። ቀሪ ግኝቶችን ደግሞ ለማስተካከል እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
በመድረኩ የተገለጹ የማስተካከያ እርምጃዎች በጽሑፍ ለዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት እንዲደርስም አስተያየት ተሰጥቷል።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) በበጀት እና ንብረት አያያዝ ችግር ክልሉ የሃብት ብክነት እየደረሰበት መኾኑን አንስተዋል።
ተቋማት በኦዲት ግኝት የተሰጣቸውን አስተያየት ተቀብለው ለማስተካከል መጀመራቸው አበረታች እርምጃ መኾኑንም ገልጸዋል። የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓትን የመዘርጋት አስፈላጊነትንም አንስተዋል።
ሥርዓቱን አክብሮ እና አሳማኝ ምክንያቶችን ይዞ ግዢ የመፈጸምን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።
ተሰብሳቢ እና ተከፋይ ገንዘብ ላይ በግልጽ መታወቅ እና መመዝገብ እንዳለበት ነው የገለጹት። በየዓመቱ ከ3 ቢሊዮን በላይ ተሰብሳቢ ገንዘብ እየተጠራቀመ ነውና ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እመቤት ከበደ በሰጡት ማጠቃለያ የተቋማትን የኦዲት ግኝት የማስተካከል ጅማሮን አበረታተዋል።
በክልሉ ተሰብሳቢ ሒሳብ በየጊዜው እያደገ የመኾኑን አሳሳቢነት አንስተዋል። ዲጂታላይዜሽንን በመጠቀም የሒሳብ እና በጀት ሥራን የማቀላጠፍ አስፈላጊነትም ጠቁመዋል።
የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር ጉድለቶችን መከላከል እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ኦዲት ለማድረግ እና አስተያየት ለመስጠት ያልተቻለባቸው “የከፋ ኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት በፍጥነት እንዲያርሙም ነው” ያሳሰቡት።
የተሰጡ አስተያየቶች እና አቅጣጫዎችን በመፈጸም ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ እና ለቋሚ ኮሚቴው በ15 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		
