
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት መነጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም የሃይማኖት አባቶችን በማሳተፍ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ሲኖራት ከኑሮ ውድነቱ ላይ የራሱ የኾነ አወንታዊ አስተዋጽኦ ያለው በመኾኑ ለዚህም ከመንግሥት ጎን ኾነው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በዘይት እና ሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታክስ እና ቀረጥ የኑሮ ውድነቱ ላይ ጫና የሚያሳድር በመኾኑ መንግሥት እንዲያየው እና መፍተሔ እንዲያስቀምጥለትም ጠይቀዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በንግድ እና በግብር ሂደት ላይ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱም አንስተዋል። በንግዱ ዘርፍ ላይ ያለው የሙስና እና ብልሹ አሠራር መፈተሽ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ምክትል ኀላፊ ስንታየሁ ታፈረ አገልግሎት በሚሠጡ ባለሙያዎች ላይ የሚታዩ የሥነ ምግባር ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ማስረጃ በተገኘባቸው ላይ እርምጃ መወሰዱንም አንስተዋል፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብም የሙስና ተባባሪ ባለመኾን እና አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ከመንግሥት ጋር መተባበር አለበት ብለዋል፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ገነት አሰፋ የንግዱ ማኅበረሰብ በሌሎች ልማቶች ግንባር ቀደም እንደኾነው ሁሉ በሰላም ላይም የበኩሉን ማበርከት አለበት ብለዋል፡፡ የባለሙያዎችን የሥነ ምግባር ችግር በቅርበት በመከታተል ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ወርቁ በውይይቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን በመውሰድ ምላሽ እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል፡፡ ችግሮችን በጋራ ተቀራርቦ በመሥራት እንፈታለን ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ኃይለ ማርያም እሸቴ የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የንግዱ ማኅበረሰብም የበኩሉን ማበርከት አለበት ብለዋል፡፡ የሰላምን ጉዳይ በመመካከር እየፈታን ሰላማዊ በኾነ መንገድ የክልሉ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና መብቶች እንዲከበሩ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት።
 የባሕር በር ጥያቄ ዋና ጥያቄዎችን ነው፤ ይህንን እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለማስመለስ ሰላም ላይ ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኑሮ ውድነቱ ሕዝብን እየፈተነ ነው፤ ይህ ደግሞ ነጋዴውንም የሚጎዳ በመኾኑ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን መታገል ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፤ ከጎኑ መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		
