የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ እና የሕዝብ ድጋፍ ያለው ነው።

19
ደብረብርሃን: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊ ነጋዴዎች የባሕር በር ጉዳይ ወሳኝ አጀንዳ መኾኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ እና በሕዝቡ ድጋፍ ያለው ነውም ብለዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተዳደረው በግብርናው ዘርፍ በመኾኑ ዘርፉን በማሻሻል የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንደሚገባም አንስተዋል።
ይህንን ለማሳካት ግን የውስጥ ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የንግዱን ማኅበረሰብ የሚያማርሩ ብልሹ አሠራር እና ሕገወጥ ንግዶች እልባት እንዲሰጣቸውም ተወያዮቹ ጠይቀዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመረ ላቀው እንደ ሀገር ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ፣ አዳዲሶቹም እየተጀመሩ እንደኾነ አንስተዋል።
ያም ኾኖ ግን አሁንም የሕዝብን ፋላጎት ሙሉ በሙሉ ማርካት ባለመቻሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ ብለዋል።
ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር መወያየት ያስፈለገው በጋራ በመሥራት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደኾነም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የፖለቲካ ምሕዳሩን ለመቀየር የተሠራው ሥራ በቀላሉ የሚታይ እንዳልኾነም ገልጸዋል። ነገር ግን ነጻነትን በአግባቡ የመጠቀም ችግር እየተስተዋለ ነው ብለዋል።
የባሕር በር ባለፉት ዓመታት ከተራ ሸቀጥ ጋር እንዲነጻጸር ሲደረግ መቆየቱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው
አሁን ግን የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ ሁሉም ይህንን ዕውነታ ሊረዳ ይገባል ነው ያሉት።
የሰላም ሥራ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ አለመኾኑንም ገልጸዋል። ሁሉም የሚጠበቅበትን ኀላፊነት መወጣት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ብልሹ አሠራር እንዲፈጸም ከአገልግሎት ሰጭው ባልተናነሰ አገልግሎት ፈላጊውም ተባባሪ ሲኾን ይታያል ብለዋል።
ይህንን ችግር ለማስቀረት የመሪዎችን አቅም ከመገንባት እና በአጥፊዎች ላይ ርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን አገልግሎት ፈላጊዎችም ብልሹ አሠራርን በማጋለጥ እና ተባባሪ ባለመኾን ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደም ግፊት በሽታ እንዴት ይከሰታል?
Next article‎ለማር ምርት ጥራት ይጠነቀቃሉ ?