
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደም ግፊት እና የደም ግፊት በሽታ ይለያያል። ደም ግፊት የሚባለው ልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ህዋሶች ደም በምትረጭበት ወቅት በደም ሥሮች ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ኀይል ነው።
ልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ደም በምትረጭበት ወቅት ከአቅሟ በላይ ደም ለመርጨት የሚያጋጥማት ኀይል ወይም ሞገድ ደግሞ የደም ግፊት በሽታ እንደሚባል የመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር መንግሥቱ ይደግ ገልጸዋል።
ደም ግፊትን ለማወቅ ሁለት ዓይነት ሲስቶሊክ እና ዲያስቶክ የተባሉ መለኪያ ቁጥሮች አሉ። ሲስቶሊክ የላይኛው መለኪያ ቁጥር ሲኾን ዲያስቶሊክ ደግሞ የታችኛው መለኪያ ቁጥር ነው።
እንደ ዶክተሩ ገለጻ የዓለም ጤና ድርጅት(WHO) እንዳረጋገጠው ሲስቶሊክ 140 ኤምኤል ሜርኩሪ እና ከዛ በላይ ከኾነ እና ዲያስቶሊክ ደግሞ 90 ኤምኤል ሜርኩሪ እና ከዛ በላይ ሲኾን አንድ ሰው የደም ግፊት በሽታ አለበት ይባላል ብለዋል።
ነገር ግን በአንድ ልኬታ ብቻ ግፊት አለ ብሎ መናገር እንደማይቻል ጠቁመዋል።
ሰዎች ዕድሜያቸው በጨመረ ቁጥር የግፊት በሽታ የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም በዕድሜ መጨመር ሰበብ የደም ቅዳዎች ግፊት ስለሚቀንስ፣ በደም ስሮች ውስጥ የስብ መከማቸት ስለሚኖር እና ልብ በምትመታበት ጊዜ የልብ ጡንቻዎች የኮማተር እና የመለጠጥ ኹኔታ ስለማይፈጥሩ በዚህ ጊዜ የግፊት በሽታ እንደሚከሰትባቸው ዶክተሩ አብራርተዋል።
ጤናማ ያልኾነ የአመጋገብ ሥርዓት ለግፊት በሽታ ያጋልጣል። ጨው እና ቅባት የበዛበት ምግብ አብዝቶ መጠቀም፣ አዘውትሮ አልኮል መጠጦችን መጠቀም፣ ሲጋራ ማጨስ፣ በቂ የኾነ የሰውነት አንቅስቃሴ አለማድረግ እና የመሳሰሉት ለግፊት ሕመም መነሻ ምክንያት ናቸው።
አንድ ሰው የደም ግፊት በሽታ ከተገኘበት በኃላ ሐኪም የከለከለውን ምግብም ኾነ መጠጥ መጠቀም እና ሲጋራ ማጨስ የለበትም። የታዘዘለትን መድኃኒትም በአግባቡ መውሰድ እና በአቅራቢያው በሚገኝ ጤና ተቋም ክትትል ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።
ስትሮክ ከደም ግፊት ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰት በሽታ ነው። ስትሮክ የሚከሰተው ድንገተኛ የኾነ በአንጎል ውስጥ ባሉ የደም ስሮች ውስጥ የሚፈሰው ደም ሲያቆም ወይም በጭንቅላት ውስጥ ያሉ ደም ስሮች ሲፈነዱ ይህን ጊዜ ስትሮክ ይከሰታል።
ነገር ግን በአደጋ ጊዜ ጭንቅላት ውስጥ የሚፈስ ደምን አያጠቃልልም ነው ያሉት።
እንደስፔሻሊስቱ ገለጻ ስትሮክ ሲከሰት የአፈ መጣመም፣ በአንድ በኩል ያሉ የሰውነት ክፍሎች እጅና እግር አለመታዘዝ፣ የዕይታ መቆም እና የአነጋገር ችግር መከሰት የተወሰኑ ምልክቶች ናቸው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በደም ግፊት በሽታ በብዛት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ይጠቃሉ። ምክንያቱም ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ በሲጋራ ሱስ፣ በብዛት አልኮል መጠጦችን በመጠጣት እና መሰል ነገሮችን አብዝተው በመጠቀም ለበሽታው ተጋላጮች መኾናቸውን አስረድተዋል።
የግፊት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ሐኪም የከለከላቸውን ምግብም ኾነ መጠጥ አለመጠቀም፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና የታዘዘን መድኃኒት በሥርዓት መውሰድ እንዳለባቸው ዶክተር መንግሥቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		
