የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ምን እየተሠራ ነው ?

8

ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ መና ተከስተ እና ተማሪ ትዕግስት አደሩ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሠቆጣ ከተማ የአዝባ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው። በትምህርት ቤቱ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችም ናቸው።

በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ የኾነ የተማሪዎች መጨናነቅ እንዳለ እና ክፍሎቹ ከአቅማቸው በላይ ተማሪዎቹን መያዛቸውን ገልጸዋል።

በትምህርት ዘመኑ የመማረያ መጽሐፍትን ጨምሮ ሌሎች ለመማር ማስተማር ተግባሩ መሳለጥ ወሳኝ የኾኑ ቁሳቁስ እንዳልተሟላላቸው ተናግረዋል።

ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሠራ ክፍል ውስጥ በመማራቸው እና በቂ ወንበር ባለመኖሩ ምክንያት የትምህርት አቀባበላቸው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

የአዝባ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ገብረ መስቀል አሰፋ በ2018 የትምህርት ዘመን ከተያዘው ዕቅድ በላይ ተማሪዎችን መቀበላቸውን ተናግረዋል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመጀመሪያው ነገር ግብዓት ነው ብለዋል።

ግብዓት ሲባል የተማሪ ክፍል ጥምርታ ተመጣጣኝ ከመኾን ይጀምራል ነው ያሉት። ትምህርት ቤቱ ከአቅሙ በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል እንደተገደደም አስረድተዋል።

በቂ የመማሪያ ክፍል፤ መጻሕፍት፤ ሰሌዳ፣ ወንበሮች እና መምህራን እንዳልተሟሉለት አንስተዋል። ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ቤት አለ ለማለት እንደሚቸገሩም ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቱ ከማኅበረሰቡ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች በሚያገኝው ገቢ የተወሰኑ ችግሮችን ለመፍታት ሙከራ ቢያደርግም ችግሮቹን ግን መቅረፍ አለመቻሉን ገልጸዋል።

ጥራት መለኪያ አለው፤ በተለይም የትምህርት ቤቱን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ ተማሪዎችን ተወዳዳሪ እና ብቁ ለማድረግ የትምህርት ቤቶች ጥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፈ ሞገስ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር መንግሥት ከሚያደረገው ድጋፍ በተጨማሪ የዞኑን ማኅበረሰብ እና ረጅ ድርጅቶችን በማሳተፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት ምሕዳርን መፍጠር ወሳኝ ነው ያሉት ኀላፊው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ከመገንባት ጀምሮ የትምህርት ቁሳቁስን ለማሟላት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች መኾናቸውን አንስተዋል። ከደረጃ በታች ሲባል ደረጃ 1 እና 2 ላይ የሚቀመጡ ናቸው ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በማሻሻል ደረጃ 3 እና 4 ላይ ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት ማሻሻል መርሐግብር ባለሙያ አንዱዓለም ጤናው እንደገለጹት የትምህርት ጥራት በርከት ባሉ ጉዳዮች የሚገለጽ ነው።
ባለፉት ዓመታት ትምህርት ቤቶች ብዙ ጉዳቶች ደርሶባቸው ስለነበር የግብዓት መጓደል በሰፊው ይታይባቸዋል ነው ያሉት።

እንደ ክልል ትምህርት ቢሮ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ የመጀመሪያ ሥራ እንደኾነም ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ካልኾኑ በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርሳሉ ነው ያሉት።

ትምህርት ከመጀመሩ በፊትም በክረምት ወራት በበጎፍቃድ ሥራ ከተሰማሩ ወጣቶች ጋር በጋራ በመኾን ትምህርት ቤቶችን ምቹ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

ከመማሪያ፣ ከወንበር፣ ከቤተ መጽሐፍት እና ከቤተ ሙከራ ጥገናዎች ጉን ለጎን ደግሞ የአቅም ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎችን በመለየት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በትምህርት ቤት ውስጥ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

የጥራት መለኪያ ውጤት ነው ያሉት ባለሙያው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጥራትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፦ ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እውነተኛውን የሀገራችን ለውጥ የሚመራው የራሳችን ጽናት፣ ፈጠራ እና የሥራ ትጋት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)