
ሰቆጣ: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራን እና የአጎራባች ወረዳዎችን በጤናው ዘርፍ እያገለገለ የሚገኘው ተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ካሉበት ችግሮች ውስጥ የመድኃኒት እጥረት ቀዳሚው ነው።
ወይዘሮ አበባ ሰፊው የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ ልጃቸውን ለማሳከም ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ ይናገራሉ።
የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል እንዳለው ተናግረዋል።
ወይዘሮ አበባ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ቢኾኑም ከሆስፒታሉ መድኃኒት ባለመኖሩ ከግል በከፍተኛ ገንዘብ መድኃኒት እንደገዙ ጠቅሰዋል።
የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለሙያ ዮሐንስ ደምሴ ማኅበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል የሕክምና ባለሙያዎች በተነሳሽነት እየሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ የመድኃኒት፣ የተኝቶ ሕክምና መስጫ እና የድንገተኛ ክፍል እጥረቶች መኖራቸውን ባለሙያው ለአሚኮ ገልጸዋል።
የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ያለበትን የመድኃኒት እጥረት ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጂ ታምሩ ቢምረው ተናግረዋል።
ከ120 በላይ የሚኾኑ የመድኃኒት አይነቶችን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መድኃኒት መግዛታቸውን ጠቁመዋል።
ሥራ አሥኪያጁ የማኅበረሰቡን አገልግሎት ለማፋጠን ሲባል የመድኃኒት ግዥን በብድር ጭምር እንደገዙ ነው ያብራሩት።
ሆስፒታሉ የግብዓት ግዥ በመፈጸሙ ምክንያት ምርመራ የሚደረግባቸውን የሕክምና አይነቶችን ከ65 ወደ 85 ማሳደግ መቻሉ ነው የተገለጸው።
በቀጣይም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልገሎት ለመስጠት የተቀናጀ ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
