
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሰላም እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ ሕዝቡን እንዳስመረረው እና ከችግር ላይ ችግር እንደኾነበት ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሙሐመድ ሰኢድ የሰላም እጦቱ እየከፋ በመጣ ቁጥር የሚበላው ራሱን ኅብረተሰቡን ነው፤ ይህንን ተረድቶ ከአዙሪቱ መውጣት ያስፈልጋል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ተከታዮቻቸውን ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ልጆች ሲጣሉ ቆንጥጦ እና አስማምቶ ያልፍ የነበረ ማኅበረሰብ አሁን ሰው ሲገዳደል እያየ ዝም የሚልበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ይህም የሚጎዳው እኛን ነው ብለዋል።
አበው ”በባሕር ላይ ሂዶ ምንድን ነው ቅልውጡ ግብጾች ለሀበሻ ደግ ሰው ላይሰጡ” እንዳሉት ችግራችን ራሳችን ፈትተን ወደ ሰላማችን መመለስ አለብን ነው ያሉት። ለሰላም መንግሥት እና የሃይማኖት አባቶች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር- ደሴ ሀገረ ስብከት የጳጳሱ አማካሪ አባ ፍሬሕይዎት ገብረ መስቀል የሃይማኖት አባቶች ሥራ ቃለ እግዚአብሔርን ማስተማር እና መጸለይ መኾኑን ተናግረዋል።
ሰዎች ያላቸውን የፍላጎት መለያየትን በውይይት አለመፍታታቸው ለሰላም እጦት እንደዳረገ ጠቅሰዋል። ሕዝብም ለሰላም መትጋት እና ከልብ መጸለይ እንዳለበት አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ እና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ መላዕከ ሰላም ለዓለም ጌታሁን በሰላም እጦቱ ኅብረተሰቡ ወጥቶ ለመግባት እና ሠርቶ ለማደር እየተቸገረ መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የመንገድ መዘጋትን ማስተካከል፣ ጸጥታውን በቁርጠኝነት መምራት እና የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚያስፈልገው ነው የተናገሩት።
የሃይማኖት አባቶችም ኾነ ፖለቲከኞች የተቀመጥንበት ወንበር የሕዝብ ኀላፊነት መኾኑን ተገንዝበን በቁርጠኝነት መሥራት አለብን ነው ያሉት። ሕዝቡ ሰላም ይፈልጋል፤ አሁንም “የታጠቁ ኃይሎች ከልብ ሰላም ሊፈጥሩልን ይገባል” ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት አናጋው የባሕር ዳር ከተማ ጸጥታ አስተማማኝ መኾኑን ገልጸዋል። ሰላሙ ዘላቂ እንዲኾንም የሕዝቡ ተሳትፎ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
