
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፖሊስ ወይም ወታደር ሲባል ሀገርን መጠበቅ፣ ለሀገር መቆም፣ ራስን ለሀገር መስጠት እንደኾነ የሚታወሰን ብዙዎች ነን።
ፖሊስነት የሕዝብ እና የሀገርን ሰላም መጠበቅ እና ምቹ የልማት አካባቢን መፍጠር ነው ዓላማ እና ስሪቱ።
ይህንን ተረድተው እና ለሕዝብ ሰላም ሲሉ ሙያውን መርጠው የገቡበት እና እያገለገሉ ያሉት በርካቶች ናቸው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን የአድማ መከላከል እና መደበኛ ፓሊስ ምልምል ሠልጣኞችን ዛሬ አስመርቋል።
በዕለቱ ከተመረቁት ምልምል ሠልጣኞች መካከል ወንድማማቾቹ ኮንስታብል አፈወርቅ ያረጋል እና ኮንስታብል ጥላሁን ያረጋል ይገኙበታል።
ፖሊስነት ከራስ እና ከቤተሰብም በላይ ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ዘብ መቆም ነው ብለዋል።
የሰላም እጦት በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ኑረንበት በዓይን ተመልክተነዋል፤ ቤተሰቦቻችንን ሲፈትን አይተናል፤ ግጭት እና ጦርነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እንፈልጋለን፤ የክልሉ የጸጥታ ኀይል አባል በመኾን ሰላምን ለማስፈን ነው ወደሙያው የገባነው ብለዋል ወንድማማቾቹ።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሕዝብ አንገቱን ደፍቷል፤ እናቶች በልጆቻቸው ሞት አዝነዋል ነው ያሉት።
የተመረቁበትን የፖሊስነት ሙያ በመጠቀምም ሰላም እንዲሰፍን እና ምቹ የልማት አካባቢ እንዲፈጠር በትጋት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ሌሎች ተመራቂ ወንድማማቾች ኮንስታብል ሳለ ጠገናው እና ኮንስታብል ጌትሽ ጠገናው ናቸው። ወንድማማቾቹ እንዳሉት የቤተሰቦቻቸውን ሥራ ወደጎን በመተው እና የሀገራቸውን እና የሕዝባቸውን የሰላም ጉዳይ በማስቀደም ነው ወደ ፖሊስነት የሙያ ሥልጠና የተቀላቀሉት።
በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ሕዝብን ለችግር መዳረጉን፤ ወጥቶ ለመግባትም ማዳገቱን ተናግረዋል።
ይሄም ቁጭት እንደፈጠረባቸው እና የፖሊስነት ሙያ ሥልጠና ወስደው በማገልገል ችግሩን ለመፍታት ሲመኙ እንደነበርም ገልጸዋል። ወደ ፖሊስ ማሠልጠኛ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ሁለት ኾነው ለመግባት ባገኙት ዕድልም መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከተመረቁ በኋላም ወደ ሕዝቡ በመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
በማሠልጠኛ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ የአካል ብቃት እና የክሕሎት ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን አንስተዋል።
ወደ ሕዝብ ተመልሰው እንደሚያገለግሉ፣ በቅድሚያ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚሠሩ እና አስፈላጊውን ሁሉ የሰላም መጠበቅ ሥራ እንደሚያከናውኑም ጠቁመዋል።
ከወንድማማችነት ላይ ሀገር እና ሕዝብን ለመጠበቅ ያለመ ወታደራዊ ጓድነት ሲጨመርበት የተለየ እና ደስ የሚል ስሜት እንዳለው የገለጹት ወንድማማቾቹ በሥልጠና ወቅትም ልዩ ብርታት እና ወኔ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ሕዝብ እና ሀገሩን የሚወድ ሁሉ ሰላምን ይምረጥ፤ ሰዎች በሰላም እንዲንቀሳቀሱ እና እንዲሠሩ ይፍቀድ፤ ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት ይቆጠብ ብለዋል። ይህንን የማያደርግ አካል ካለ ግን በሕጉ መሠረት እንዲታረም እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ እንዳሉት በርካታ ቤተሰቦች ከአንድም አልፎ ሁለት እና ሦስትም ልጆቻቸውን ለፖሊስነት ሙያ ሥልጠና ሸኝተው ይልካሉ።
“ፖሊስነት ሕዝብ ሰላሙ ተጠብቆ እንዲያለማ እና ያለስጋት ተዘዋውሮ እንዲሠራ የሚያስችል ሙያ ነው” ብለዋል።
ዛሬ በሙያው የተመረቁ የፖሊስ አባላትም ተመልሰው የሚያገለግሉት ሕዝብን ነው ብለዋል። ወጣቶች ወደ ፖሊስነት ሙያ ለመቀላቀል ፍላጎት ሲያሳዩ መርቀው የሚልኩ ወላጆች እንዳሉም አንስተዋል።
ዝንባሌው ያላቸው ወጣቶች ሁሉ የሀገር ደጀን በኾነው የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ገብተው እንዲያገለግሉ መፍቀድ እና መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
