
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል እንዲለሙ ከታሰቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የጥናት እና ዲዛይን ሥራ ከተሠራላቸው ውስጥ የሽንፋ የተቀናጀ ከፍተኛ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ፕሮጀክቱ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ እና መተማ ወረዳዎችን ለማልማት ያለመ ነው። የጥናት፣ የዲዛይን እና የማማከር ሥራውን የአማራ ክልል የልህቀት፣ ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ሲያከናውን ቆይቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አብርሃም አያሌው የፕሮጀክቶችን የጥናት እና ዲዛይን ሥራ በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራት እና ወጭ ቆጣቢ በኾነ መንገድ ለማከናወን በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑም በተቀመጠው አሠራር መሠረት በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎችን እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ዲዛይኖች በተቀመጠላቸው ጊዜ ማከናወኑን በማሳያነት አንስተዋል።
በ2007 ዓ.ም የጥናት እና ዲዛይን ሥራው ተጀምሮ በጸጥታ ችግር ለዓመታት ሲጓተት የቆየውን የሽንፋ የተቀናጀ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ2017 ዓ.ም ማጠናቀቅ መቻሉን ነው የገለጹት።
የሽንፋ የተቀናጀ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግድብ በ12 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሐይቅ ይፈጠራል ብለዋል። በመተማ ወረዳ እስከ 60 ኪሎ ሜትር፣ በቋራ እና አካባቢው ደግሞ እስከ 120 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ ዋና ካናልን የያዘ እንደኾነም ገልጸዋል። ከ95 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ያለማል ተብሎ ይታሰባልም ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ልማት ሲገባም በዓመት 118 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይታሰባል ነው ያሉት።
ከመስኖ ልማት ባለፈ በዙሪያው ስድስት አግሮ ኢንዱስትሪ ማዕከላት ይኖሩታል ብለዋል። ከ50 እስከ 60 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ነው ያሉት። የሚፈጠረው ሐይቅ እና በሐይቁ የሚፈጠሩ ደሴቶች ለቱሪዝም አቅም ይፈጥራሉም ብለዋል ዋና ሥራ አሥፈጻሚው።
በዓመት 7 ሺህ 517 ኩንታል ዓሳ ማግኘት የሚያስችል እንደኾነም አቶ አብርሐም ተናግረዋል። ይህም ሥርዓተ ምግብን ለማስተካከል አቅም የሚፈጥር እንደኾነ ነው የገለጹት።
አካባቢው በረሀማ በመኾኑ የከርሰ ምድር ውኃን በማበልጸግ የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ማስተካከል ይችላል። የአረንጓዴ ልማትንም በማሳደግ ትልቅ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
የመስኖ እና የቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናት እና ዲዛይን መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር ያሬድ ሙላት የሽንፋ የተቀናጀ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተያዙ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዋነኛው ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በጸጥታ ምክንያት ለዓመታት ቢጓተትም በ2017 በጀት ዓመት ከክልሉ ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ ከጥቃቅን ሥራዎች ውጭ ያለውን የጥናት ሥራ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል። በቀጣይ በሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ አሠራር እና መርሐ ግብር መሠረት ወደ ግንባታ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ፕሮጀክቱ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ይጨርሳል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። ከመስኖ ልማት ባለፈ ለንብ እርባታ፣ ለእንስሳት ልማት፣ ለቱሪዝም፣ ለመጠጥ ውኃ፣ ለኃይል አቅርቦት እና ለመሳሰሉ የተቀናጁ የልማት ሥራዎችን የያዘ እንደኾነም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በሚሠሩ የልማት ሥራዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
