
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል የሚቲዎሮሎጅ ሳይንስ ረዳት ተመራማሪ እንደግ አንላይ ባለፋት ጊዜያት በአማራ ክልል ምዕራብ አማራ ዞኖች ላይ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደተመዘገበ ተናግረዋል።
በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር እና በጥቂት የሰሜን ጎንደር ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ አልፎ አልፎ ይመዘገባል ብለዋል።
በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደቡባዊ ዋግኽምራ እና ሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ስፍራዎችም በቀጣይ ኅዳር ወር አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይኖራቸዋል ብለዋል። አሁን ላይ በምሥራቅ አማራ አልፎ አልፎ ደመናማ የአየር ሁኔታ እየተስተዋለ መኾኑንም ነው የጠቀሱት።
በቀጣይ አምስት ቀን በአብዛኛው የክልሉ ስፍራዎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ተናግረዋል። ከዕለት ወደ ዕለት ግን እየቀነሰ እንደሚሄድ ነው የተናገሩት። ከአምስት ቀን በኋላ ደግሞ እንደሚያቋርጥ ጠቅሰዋል።
በአዊ ዞን እና በምዕራብ ጎጃም አንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ ከአምስት ቀን በኋላም አልፎ አልፎ ቀላል ዝናብ የመኖር ዕድል እንዳለውም ተናግረዋል።
በእነዚህ አምስት ቀናት የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አስቻይ ሁኔታ ላይኖር ይችላል፤ ከአምስት ቀን በኋላ ግን ዝናቡ ስለሚያቋርጥ የደረሱ ሰብሎችን ለመሠብሠብ አስቻይ ሁኔታ ይኖራል ብለዋል። አሁን ላይ እየታየ ያለው የዝናብ ሥርጭት የሚፈጥረውን ጫና ብቻ ሳይኾን ጥሩ ጎን እንዳለውም አንስተዋል።
አብዛኛው የክልሉ ስፍራዎች ላይ ከአምስት ቀን በኋላ ዝናብ የማቋረጥ አዝማሚያ ቢያሳይም እንደገና በኅዳር ወር በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ዳግም ተመልሶ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከኅዳር ወር በኋላ የበጋው ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደገና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሳይቤሪያ የሚነሳ ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር እንዲሁም ከሰሀራ የሚነሳ ደረቅ እና ሞቃት አየር ተጽዕኖ ውስጥ ክልሉ ይቆያል ብለዋል።
ይህ ከሰሀራ የሚነሳው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ጧት እና ማታ ላይ ያለውን የአየር ሙቀት በጣም እንዲቀዘቅዝ ያደርገዋል ነው ያሉት።
አማራ ክልል ላይ አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የመኖር ዕድል አለው ያሉት ተመራማሪው የሚኖረው መጠን ቀላል መኾኑን ነው የተናገሩት።
በቀጣይ ኅዳር ወር በክልሉ ደጋማ ስፍራዎች ቀለል ያለ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይጠበቃል ብለዋል። የዝናብ መጠኑ የከፋ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ እንዳልኾነም ተናግረዋል።
በአርሶ አደሮች በኩል ገና ዝናብ አለ ተብሎ በጣም ያልደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ተገቢ እንዳልኾነም ተናግረዋል። ለምርት ብክነት እንደሚዳርግም ጠቁመዋል። የአየር ትንበያ መረጃዎች ተለዋዋጭ መኾናቸውንም አንስተዋል።
በቀጣይ ጊዜያት አርሶ አደሮች በተለያዩ የመረጃ ማግኛ አማራጮች ከሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት የሚሰጡ ወቅታዊ መረጃዎችን መከታተል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
