የመስኖ ፕሮጄክቶች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው?

3
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጄክቶች ይገኛሉ። እነዚህ የመስኖ ፕሮጄክቶች ምርት በዓመት ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ እንዲመረት በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።
በአማራ ክልል ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጄክቶች መካከል በሰሜን ጎጃም ዞን የሚገኘው የቆጋ መስኖ ፕሮጄክት አንደኛው ነው። ይህ ፕሮጄክት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ፕሮጀክትም ነው።
የሰሜን ሜጫ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጥላሁን ተላከ የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ተጠቃሚ ናቸው።
የመስኖ ልማት በመኸር ያለሙት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ሰፊ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከኾኑ ጀምሮም ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱንም አብራርተዋል። የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠው ልጆቻቸውን ያለችግር በማስተማር ሥራ ማስያዛቸውንም ገልጸዋል። ጥሪት ማፍራት እንደቻሉም ይገልጻሉ፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የመስኖ ልማት እና የተፋሰስ ሥራዎችን መሥራት የግድ መኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ 1ሺህ 333 ተፋሰሶች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል አሥተዳደሪው ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ ልማትን መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት 466 ተፋሰሶችን ወደ ተግባር በማስገባት እና ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ 33ሺህ 543 ሄክታር መሬት በመስኖ እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 21ሺህ ሄክታር መሬቱ በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ነው ያስረዱት፡፡
በዞኑ የቆጋ መስኖ ልማትን በመጠቀም ከፍተኛ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እንደሚለማም ነው የተናገሩት። የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጄክት ለመስኖ ልማት ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆልቲካልቸር ልማት ዳሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የመስኖ ልማት እና የተፋሰስ ሥራዎችን መሥራት የግድ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ የሚባሉ የመስኖ ልማቶች እንዳሉም ጠቁመዋል። ዳሬክተሩ መካከለኛ ተብለው የሚጠቀሱ ከ500 ሄክታር መሬት በላይ የሚያለሙ ከ13 በላይ የመስኖ ፕሮጄክቶች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡
ከ3ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያለሙ ደግሞ አራት ታላላቅ የመስኖ ፕሮጄክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
በትላልቅ ደረጃ የሚገለጹት እንደ ርብ አይነቶቹ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ የርብ መስኖ ፕሮጄክት 14 ሽህ 700 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚችል ተናግረዋል። ነገር ግን አሁን እያለማ ያለው ወንዙን በመከተል እና የውኃ መሳቢያን በመጠቀም 50 በመቶ የሚኾነውን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የርብ መስኖ ፕሮጄክት የካናሎች ግንባታ አለመጠናቀቅ በሙሉ አቅሙ እንዳያለማ አድርጎታል ነው ያሉት።
የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጄክትም ከ7ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ሊያለማ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።
ይህም እስካሁን በመልማት ላይ ያለው 6ሺህ 500 ሄክታር መሬት መኾኑን ተናግረዋል። ቀሪው መሬት ከፍታ ስላለው የማስተካከል ሥራ ይጠይቃል ነው ያሉት። የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጄክት እንደ ክልልም ኾነ እንደሀገር ውጤታማ የመስኖ ፕሮጀክት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላልም ብለዋል፡፡
የሰረቫ መስኖ ፕሮጀክትም ሌላኛው ትልቁ ፕሮጄክት ነው። ይህ ፕሮጀክት በኤልክትሪክ የውኃ መሳቢያ በመጠቀም 4ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ ታቅዶ አሁን ላይ 1ሺህ 500 ሄክታር መሬት እያለማ መኾኑን ገልጸዋል።
ከእቅዱ አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡ ይህ የኾነበት ምክንያትም የተሠሩ ካናሎች ተሟልተው ባለመጠናቀቃቸው ነው ብለዋል።
ቆቦ ጊራና መስኖ ፕሮጄክት ሌላው የክልሉ አቅም መኾን የሚችል ፕሮጄክት ነው። ቆቦ ጊራና መስኖ ፕሮጀክት ሰፊ መሬት እና አካባቢ ማልማት እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ ያሉት ዳሬክተሩ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እስከ 4ሺህ ሄክታር መሬት በቀላሉ ማልማት ይችላል ብለዋል፡፡
ይህም ማልማት ከሚጠበቅበት 50 በመቶ የሚኾነውን ብቻ እያለማ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ይህ የኾነበት ምክንያትም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ መካከለኛ ተብለው የሚነሱ ብዙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። እነዚህን አቅሞች በመጠቀም በክልሉ በ2018 ዓ.ም በአንደኛ ዙር በነባር 331ሺህ 900 ሄክታር መሬት፣ በአዲስ 51ሺህ 800 ሄክታር መሬት አካባቢ የሚጠጋ በአጠቃላይ ከ383 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጀት ዓመቱ ይለማል ተብሎ በዕቅድ መያዙንም ነው የገለጹት፡፡
በሁለተኛ ዙር ወደ 122ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ ታቅዷል፡፡ ከዚህም 52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን ነው የተናገሩት።
በባለፈው በጀት ዓመት 46 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል ያሉት ዳይሬክተሩ የዚህ ዓመት ዕቅድ ከባለፈው ዓመት ምርት ጋር ሲነጻጸር የ6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡
የመስኖ ልማት እቅዶችን ለማሳካት፣ ፕሮጀክቶች ዕድሜያቸው እንዲቀጥል፣ የሚገነቡትም በፍጥነት ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እና የሚጠበቅባቸውን ያክል እንዲሠሩ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleማኅበረሰቡ አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ ከማቅረብ ይልቅ ለመብቱ መቆም አለበት።
Next article“የደረሱ ሰብሎችን ለመሠብሠብ የሚመች የአየር ሁኔታ ይኖራል”