ነጻ የሕግ ድጋፍ ምንድን ነው?

6
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ነጻ የሕግ ድጋፍ ማለት በኢኮኖሚ አቅም ማነስ እና በጉዳት ተጋላጭነታቸው ምክንያት የፍትሕ መጓደል የደረሰባቸው ዜጎች ለጥብቅና አገልግሎት ክፍያ ሳይከፍሉ በነጻ የሕግ ሙያ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግበት የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡
በአማራ ክልል ፍትሕ በሮ የፍትሐ ብሔር ፍትሕ አሥተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መንበሩ ማናየ ነጻ የሕግ ድጋፍ የአሠራር ሥርዓት የሚሰጠውን የሕግ አገልግሎት አይነት፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን እና የዚህን አገልግሎት የአሠራር ሰንሰለት የሚያመላክት ጉዳይ ነው ይላሉ።
የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በኢኮኖሚ አቅማቸው እና በሕግ ዕውቀታቸው ምክንያት ፍትሕ ሊዛባ የሚችልበት ሁኔታ ሲኖር በነጻ የሚሰጥ የፍትሕ አገልግሎት ስለመኾኑ በኢፌዴሪ የወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ፖሊሲ ቁጥር 1/4፣ 4/7 እና 4/7/1 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠ አቶ መንበሩ አመላክተዋል።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 እና 20/5፣ በኢፌዴሪ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 172 እና 174/4 ላይም እንደተጠቀሰ ገልጸዋል። በአዋጅ ቁጥር 280/2014 አንቀጽ 28 /9 እና በሌሎች የሀገሪቱ ሕግጋት ላይም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ነጻ የሕግ አገልግሎቱ በፍትሐ ብሔርም ይሁን በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር በቅድመም ኾነ በድኅረ መከላከል ጊዜ ለተከሰሱ ሰዎች የሚሰጥ የፍትሕ አገልግሎት ነው ብለዋል ለአሚኮ በሰጡት መረጃ፡፡
አገልግሎቱ በመርሕ ደረጃ በመንግሥት የሚሰጥ ሲኾን በልዩ ሁኔታ ግን በሕግ ባለሙያዎች፣ በጠበቆች እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶችም ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ለጥብቅና አገልግሎት ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ዜጎች የፍትሕ መጓደል እንዳይደርስባቸው ለመታደግ፤ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፤ በእኩልነት የመዳኘት መብትን ዕውን ለማድረግ እና በፍርድ ሂደት የተከሰሱ ሰዎችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰጥ እንደኾነም ነው የተነተኑት።
በመርሕ ደረጃ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መኾናቸውን እና ያለምንም ልዩነት እኩል የሕግ ጥበቃ የተቸራቸው መኾኑን፣ ክርክሮች ተከራካሪ ወገኖች በተገኙበት የመዳኘት መብትን የሚያጎናጽፍ ተግባር መኾኑን አንስተዋል።
ማንኛውም ሰው በግል ወይም በመረጠው ጠበቃ የመወከል መብትን የሚያረጋግጥ ስለመኾኑ፣ ጠበቃ ከሌለው በሕግ አማካሪ የመታገዝ መብት ስለመኖሩ፣ ትክክለኛ ፍትሕን የሚያጓድል ኾኖ ሲታይ እና በገንዘብ አቅሙ ምክንያት ፍትሕ የሚጓደል በሚኾንበት ጊዜ ደግሞ ገንዘብ ሳይከፍል ጠበቃ የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ አገልግሎት እንደኾነም አስገንዝበዋል።
በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ሰነድ በአንቀጽ 7፣ 8 እና በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ሰነድ በአንቀጽ 14/3 ላይም በግልጽ ተመላክቷል ነው ያሉት፡፡
ሌላው የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መርሕ በዕኩልነት የመዳኘት መርሕ ሲኾን ይህ መርሕ በተከራካሪ ወገኖች መካከል ያለውን የሕግ ዕውቀት እና የገንዘብ አቅምን ሚዛኑን ባስጠበቀ ሁኔታ በእኩልነት ለመዳኘት የሚያስችል መርሕ እንደኾነም ነው አቶ መንበሩ የገለጹት፡፡
ለጠበቃ ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ዜጎች ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ይዘው በሚቀርቡበት ጊዜ በባለሙያ ካልታገዙ በሌላኛው ወገን ብልጫ ወይም የበላይነት ሊወሰድባቸው የሚችል ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ፍትሕ እንዳይጓደል ለማድረግ የነጻ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ይህም በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ሰነድ በአንቀጽ 2፣7 እና በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ሰነድ በአንቀጽ 2/1 እና 26 ላይ ተመላክቷል ይላሉ፡፡
ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ማግኘት በራሱ ሰብዓዊ መብት ባይኾንም ሰብዓዊ መብቶችን ለማሥፈጸም ግን ወሳኝ ሚና ያለው አገልግሎት እንደኾነ ነው የገለጹት።
የፍትሕ ሚኒስቴርም በአዋጅ ቁጥር 1263/2022 አንቀጽ 40/1 እና ጠቅላይ ዐቃቤያን ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/4/ሠ መሠረትም ጉዳዩ ተቀምጧል ነው ያሉት።
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ክስ ለመመሥረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ እንደሚከራከር በግልጽ ተመላክቷል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እና ገንዘብ ከፍለው መከራከር የማይችሉ አቅም የሌላቸው የወንጀል ሰለባዎች፣ የአደጋ ተጋላጭ የኾኑ ሕጻናት፣ አቅመ ደካማ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የኤችአይ ቪ ኤድስ ሕሙማንን ወክሎ
የሚከራከር አካል የተፈቀደ መኾኑንም አንስተዋል።
ይህም በፍርድ ቤቶች እና በሌሎች የዳኝነት አካላት ዘንድ ክስ እና ክርክር በማድረግ መብት እና ጥቅማቸውን የሚያስከብር አካል ስለመኾኑ የአሥፈጻሚ አካላትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 280/2014 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 9 ላይ ተደንግጓል ብለዋል፡፡
ነጻ የሕግ አገልግሎት አሠራሩ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ በአማራ ክልል ተግባር ላይ ሲኾን በርካታ ነጻ የሕግ አገልግሎት የተሠጠ ስለመኾኑም አቶ መንበሩ ገልጸዋል።
በዐቃቤ ሕግ የሚሰጠው የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሰሜን ሸዋ ዞን በኢንቨስትመንት ዘርፍ ልምድ የሚቀሰምበት ነው።
Next articleማኅበረሰቡ አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ ከማቅረብ ይልቅ ለመብቱ መቆም አለበት።