
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ ማምረት እስከጀመሩት ድረስ 1ሺህ 519 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።
የሰሜን ጎጃም የኢንቨስትመንት ቦርድ መሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን በአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ እና በቡልጋ ከተማ አሥተዳደር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ መኳንንት ልጅ ዓለም የሰሜን ሸዋ ዞን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሞክሮ ያለው ስለመኾኑ መመልከት ችለናል ብለዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብዙ ፀጋዎች ያሉት ቢኾንም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በሚፈለገው ልክ ሥራዎች አልተሠሩም ነው ያሉት።
መምሪያ ኀላፊው የሰሜን ሸዋ ዞንን ልምድ መውሰድ የተፈለገበት ምክንያት ሰሜን ጎጃምን ባለው ፀጋ ልክ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በቁጭት ወደ ሥራ ለመግባት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሠፋ ጥላሁን በበኩላቸው የኢንቨስትመንት ዘርፉን ዓላማዎች ለማሳካት ከወረዳ እስከ ዞን ያለው መሪ እና ባለሙያ በቅንጅት እንደሚሠሩ የሚያሳዩ መሬት ላይ ያሉ እና የሚታዩ ማሳያዎችን መመልከት እንደቻሉም አስረድተዋል።
ዞኑ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች የአካባቢው ጥሬ እቃዎችን የሚጠቀሙ እና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድልን የፈጠሩ ስለመኾናቸው እንደተመለከቱ ገልጸዋል፡፡
ኢንቨስትመንት አገልጋይነትን፣ ቅንጅታዊ አሠራርን፣ ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን፣ ሰላም እና ልማት ወዳድ ማኅበረሰብን ይፈልጋል ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ደምሰው መንበሩ ናቸው።
አቶ ደምሰው ለክልሉም ኾነ ለሀገር አቅም መኾን የሚቻለው አንዱ አካባቢ ያለው ተሞክሮ በሌሎች አካባቢዎችም ሲሰፋ ነው ብለዋል፡፡
ጉብኝቱ የሰሜን ጎጃም ዞን ከሰሜን ሸዋ ዞን መልካም ልምዶችን ወስዶ ወደ አካባቢው ለማስፋት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ የወሰደበት እንደኾነም አስገንዝበዋል።
በዞኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ 51 ነጥብ 7 በመቶው አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደኾኑም አብራርተዋል።
በዞኑ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ለ68 ሺህ 644 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
