
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ሰዎች የፊት ጭምብል (ማስክ) ሳያደርጉ እንዳይወጡ አስገዳጅ መመሪያ አስተላልፋለች፡፡
የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱ ዜጎች በተለይ ከቤት ሲወጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይለብሱ እንዳይንቀሳቀሱ አስገዳጅ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ናና አኩፉ አዶ ፖሊስ መመሪያውን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ አስተላፈዋል፡፡
ጋና የጤና ሚኒስትሯ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡንም አስታውቃለች፤ ፕሬዝዳንቱ እንዳስታወቁት የ64 ዓመቱ የጤና ሚኒስትሩ ክዋኩ አጂማን ማኑ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል፤ በመልካም ሁኔታ ግን ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በጋና እስካሁን 11 ሺህ 964 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፣ የ54 ሰዎች ሕይወትም ተቀጥፏል፣ 4 ሺህ 258 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸው ተገልጿል፡፡
በሀገሪቱ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንደሚላላ፣ ትምህትርት ቤቶች ለተመራቂ ተማሪዎች ብቻ ዛሬ ክፍት እንደሚደረጉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ድንበሮቿ ግን አሁንም ዝግ ሆነው ይቆያሉ ነው የተባለው፡፡
ጋና እስከ 31 ሚሊዮን ከሚገመተው የሕዝብ ቁጥሯ ለ250 ሺህ ሰዎች ምርመራ ማካሄዷንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡