
እንጅባራ: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 46ኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በዓሉ በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች እና በፓናል ውይይት ነው የተከበረው።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳዳር ገንዘብ መምሪያ ኀላፊ መለሰ አዳል ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ የበርካታ ሰው ሠራሽ፣ ተፈጥሮአዊ እና ባሕላዊ የመስህብ ሃብቶች ባለቤት መኾኑን ተናግረዋል።
እነዚህን የመስህብ ሃብቶች በአግባቡ በማጥናት፣
በማልማት እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።.
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ሰውነት ሽፈራው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ እንደጎዳው ተናግረዋል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱንም ገልጸዋል።
የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው አካባቢዎች የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል።
በከተሞች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት በማሻሻል የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የተጀመሩ ሥራዎች ለውጥ እየታየባቸው እንደኾነም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
