
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) የግብጽ ዓየር መንገድ ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ ሁሉንም የአውሮፕላን ማረፊያዎቹን ለዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ትናንት ሰኔ 7/2012 ዓ.ም እንደገለጹት በኮሮናቫይረስ መስፋፋት ምክንያት የተዳከመው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያገግም ለማድረግ ነው በረራውን እንደገና ለመጀመር የተወሰነው፡፡ ሚኒስትሩ ሙሐመድ ማናር ከቱሪዝምና ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስረዱት ውሳኔው የውጭ ሀገራት ጎብኝዎችን ቁጥር በመጨመር የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
አውሮፕላኖቹ በጸረ ቫይረስ ኬሚካሎች በጥንቃቄ መጸዳታቸውን የገለጹት የሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትሩ በጉዞ ጊዜ የሚፈቀዱ ምግቦች ደረቅና የታሸጉ፣ መጠጦችም እንዲሁ በጠንካራ ብረት ነክ ቁሶች የታሸጉ መሆን እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡ በበረራ መርሀ ግብሮቹ ምንም ዓይነት የኅትመት ውጤቶችን መያዝም ሆነ ማሠራጨት እንደማይቻልም በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
የባህልና ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ካሊድ አል አናኒ እንደገለጹት ደግሞ የዓለም አቀፍ በረራው እንደገና ሲጀመር ዝቅተኛ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ያለባቸው ደቡባዊ ሲናይ፣ ቀይ ባሕር እና ማትሮህ የተባሉ ሦስት የባሕር ዳርቻ ክፍለ ግዛቶች ለውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ክፍት ይደረጋሉ፡፡ ሦስቱ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች የዓለም ሀገራት ጎብኝዎች ተመራጭ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የጤና ሚኒስቴር የጥንቃቄ ምክሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም አስታውቀዋል፡፡
ሀገሪቱ ከ230 በላይ ሆቴሎች ቀድሞ ያስተናግዱ ከነበረው የሰዎች ብዛት 50 በመቶ በመቀነስና ተገቢውን የንጽሕና አጠባበቅ ምክረ ሐሳቦች በመተግበር ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መፍቀዷንም ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ግብጽ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱን ተከትሎ ካለፈው መጋቢት 10/2012 ዓ.ም ጀምሮ ነበር ዓለም አቀፍ በረራዋን ያቋረጠችው፡፡
የኮሮናቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሰኔ 8/2012 ዓ.ም ድረስ በግብጽ 44 ሺህ 598 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 1ሺህ 575 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፤ 11 ሺህ 931 ሰዎች ደግሞ ማገገማቸው ታውቋል፡፡
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡