
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) አራት የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት አህጉሩን በመወከል ከመድኃኒት አምራች ኩባንያው አስትራዜኒካ ጋር የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተዋውለዋል፡፡ በቂ ክትባት በማምረት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያለመ ውል መሆኑን የጣልያን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የእንግሊዝና ስዊድን ጥምረት የሆነው ግዙፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አስትራዜኒካ 400 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባቶችን ለአውሮፓ የሚያመርት ይሆናል፡፡ ክትባቱ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየበለጸገ የሚገኝ ነው፡፡ ኩባንያው ወረርሽኙን ለመከላከል ያለምንም ትርፍ ክትባቱን እንደሚያቀርብም አስታውቋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ክትባቱ ክሊኒካዊ ሙከራ (የሕክምና ሙከራ) ላይ ነው፡፡ በዚህ ክረምት ሙከራው እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡ የሙከራ ውጤቶቹ ደኅንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ መሆኑ የክትባት ተቆጣጣሪ አካላትን ካሳመነ በአውሮፓውያኑ 2020 መገባደጃ ክትባቱን ለሰዎች ለመስጠት ታቅዷል፡፡
ኩባንያው አዲስ የገባው የውል ስምምነትም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድና ጣሊያንን ባቀፈው ከአውሮፓው የክትባት ጥምረት ቡድን ጋር የተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት ክትባቱን ለአውሮፓ አባል ሀገራት የሚያቀርቡም ይሆናል፡፡
ኩባንያው ከዚህ ቀደምም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል፤ ቻይና፣ ብራዚል፣ ጃፓንና ሩሲያም ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው ሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡
አስትራዜኒካ ሁለት ቢሊዮን ብልቃጥ ክትባቶች እንዲያመርቱለት ከዓለም አቀፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋርም ስምምነት ማድረጉን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡